You are here: HomeARTICLES‹‹ወገቤን ጠበቅ ያደረግኩት ራያ ቢራ እንዳይቋቋም ታጥቀው በመነሳት የፎከሩ ስለነበሩ ነው›› አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር

‹‹ወገቤን ጠበቅ ያደረግኩት ራያ ቢራ እንዳይቋቋም ታጥቀው በመነሳት የፎከሩ ስለነበሩ ነው›› አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር Featured

Published in Articles
Rate this item
(3 votes)

ሪፖርተር ጋዜጣ ባወጣው እትሙ አንድ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊን እንግዳው አድርጎ ነበር፡፡ አጠቃላይ ጽሁፉን ስመለከት መገረሜን ተከትሎ ብዙ ነገር ወደ ሃሳቤ መጣ፡፡ እንግዳው አቶ ዳዊት ገብረ እግዚያህሔር ይባላሉ፡፡ የራያ ቢራ ከፍተኛ አክሲዬንን በመግዝት ምናልባትም በሃገራችን የአክሲዮን ገበያ ሪከርድ የሰበረ ግዥ ሳይፈጽሙ እንዳልቀሩ ተገንዝቤያለሁ፡፡
የራያ ቢራ እውን እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉት እኝህ ሰው በሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎችም ለኪሳቸው ሳይሆን ለህዝባቸው ትርፍ እየሰሩ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ለአመታት በውጭ ሃገር ሰርተው ያካበቱትን ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ከራስ ይልቅ ሃገርን የሚያስቀድሙ አቶ ዳዊትን አይነት ግለሰቦች ዛሬም ሃገሬ ባለማጣቷ ወገናዊ ኩራቴ ጨመረ፡፡
ግን ደግሞ እንዲህ ከራስ ይልቅ ለወገን የሚሉት ብቅ ብቅ ሲሉ ጋሬጣ የሚያኖሩ ስግብግብ ኪራይ ሰብሳቢዎች መኖራቸው በእርግጥ ለእድገት ሩጫችን መሰናክል፣ ለብልጽግናችን ከል መሆናቸው እሙን ነው፡፡ በዲያስፖራው መካከልም ከእድገት ይልቅ ውድቀት የሚናፍቃቸው ብዙ ናቸውና ከአቶ ዳዊት ተሞክሮ ብዙ ሊማሩ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ሃገር ከመዝረፍ እና ለኔ ከማለት ለእኛ ወይም ለወገኔ ማለት ምንኛ ቁርጠኝነት ምንኛ ሃገር ወዳድነት መሆኑን ሪፖርተር ያስነበበውን ቃለ ምልልስ አንብበው እንዲረዱት እነሆ ሙሉውን ጽሁፍ አቅርበነዋል፡፡

‹‹ወገቤን ጠበቅ ያደረግኩት ራያ ቢራ እንዳይቋቋም ታጥቀው በመነሳት የፎከሩ ስለነበሩ ነው››

አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር፣ የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ከፍተኛ ባለድርሻ
አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ የ62 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡ ሰሞኑን የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ካፒታል ለማሳደግ በወሰነው ውሳኔ በግለሰብ ደረጃ ትልቁን አክሲዮን ለመግዛት ወስነዋል፡፡ ቀደም ሲል የ55 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ገዝተዋል፡፡
ቀጥሎ ደግሞ አጠቃላይ ግዥውን ወደ 125 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ወስነዋል፡፡ ይህ ውሳኔ ሰሞነኛ መነጋገሪያ ነበር፡፡ ይህንን ያህል ገንዘብ ከየት መጣ? የሚል ጥያቄ እየተሰነዘረ ነው፡፡ ዓደዋ ተወልደው ዓደዋ ያደጉት አቶ ዳዊት በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ በሶሻል ሳይንስ አድቫንስ ዲግሪ አላቸው፡፡ በመምህርነትም ሠርተዋል፡፡ ከዚያም ከ32 ዓመታት በፊት ከአስመራ ወደ ሱዳን ከዚያም አቡዳቢና ዱባይ ሄደው ነዋሪ ሆነዋል፡፡ የሀብት ምንጫቸውም የተገኘው እዚያው በነበሩት ወቅት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸውንና አሁን የደረሱበትን ደረጃ በተመለከተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አስተዳደግዎን በአጭሩ ይንገሩኝ?

አቶ ዳዊት፡- የተወለድኩትና ያደጉት ዓደዋ ነው፡፡ ከቤተሰቦቼ እንደምሰማሙ በልጅነት ዘመኔ ፀባዬ የተለየ ነበር፡፡ ጥያቄ ታበዛ ነበር ይሉኛል፡፡ ያልገባኝን ነገር ደጋግሜ እጠይቃለሁ፡፡ ከፍ ካልኩ በኋላ በራሴ የምታዘባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ በአቅሜ መመራመር አበዛ ነበር መሰለኝ፡፡ አስፈላጊ ይሁን አይሁን ባላውቅም በልጅነቴ መጠጥ ጠጥቼ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ሰው ሰክሮ አየሁ፡፡ ስካርን ለማወቅ በ12 ዓመቴ ጠጥቼ ወላጆቼ ፊት ሰከርኩ፡፡ ይህንን ያደረኩትም ሰው ከሰከረ የሚያደርገውን ነገር አያውቅም ለሚለው መልስ ለማግኘት ነው፡፡ ራሴን ሳትኩ፡፡ ያቺ ዓይኔን ጨፍኜ ፊሊተርና ጠጅ የጠጣሁባት በቅል የተሠራች መጠጫ ለታሪክ እስካሁን ድረስ አለች፡፡

ሌላው ሃይማኖት ብዙ አላጠብቅም እንደ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ አልጾምም፡፡ ይህ የሆነው ጐረቤታችን ያሉ ሙስሊሞች አጿጿምና ኢቫንጀሊካል ትምህርት ቤት ገብቼ ያየሁት ከኦርቶዶክስ አጿጿም ጋር ስለተምታታብኝ ነው፡፡ በአንድ ወቅት እናትና አባቴ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ሲመለሱ እኔ ቁርሴን እንቁላል ስበላ ነበር፡፡ አባቴ እንዴት አትጾምም ብሎ ጮኸብኝ፡፡ እኔም ለምን እጾማለሁ አልኩት፡፡ እሱ የሚችለውን ሁሉ ሊያስረዳኝ ሞከረ፡፡ እኔ ደግሞ መጾም ካለብኝ እንደ አቶ አብዱ ልጆች ነው አልኩት፡፡ ተቆጣኝ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ አባቴ ያኔ ጾምን በሚመለከት ያልከኝ ትዝ ይልሃል አለኝ፤ አዎ! አልኩት፡፡ ትክክል ነህ አለኝ፡፡ መጾም ከሁሉም ነገር መቆጠብ ነው አለኝ፡፡ እንዲህ ዓይነት ባህሪዎች ነበሩኝ፡፡ የራሴን መንገድ ነው መከተል የምፈልገው፡፡ በትዕዛዝ የምሠራው ነገር የለም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ በኋላ አስተማሪ ሆንኩ፡፡ በመምህርነት የሚያዝህ ሥራህ ብቻ ነው፡፡ ነፃነት ሰጠኝ፡፡ ያው የትግራይ ሰው አብዛኛው የንግድ ባህሪ የለውም፡፡ በተለይ ክርስቲያኑ፡፡ ስለዚህ ወደ ቢዝነስ የሚያስገባኝ ነገር አልነበረም፡፡ ግን ሁሉም እንደሚያውቀው ሕይወት ውሳኔ አላት፡፡ የትግሉ ሁኔታ ሲጀመር ሁኔታዎች ምቹ አልነበሩም፡፡ ጐንደርና አዲስ አበባ ሠርቻለሁ፡፡ ያለንበት ሁኔታ ጥሩ አልነበረም፡፡ ገዳይህና ወዳጅህ አይታወቅም፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ተቀየርኩ፡፡ መጨረሻ አስመራ ተመደብኩ ከዚያም እ.ኤ.አ. በ1979 መጨረሻ ወደ ሱዳን ገባሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ክትትል ነበረብዎት? ብዙ ችግር እንደነበር ገልጸውልኛል፡፡ ከአስመራ ወደ ሱዳን እንዴት ሄዱ?

አቶ ዳዊት፡- በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ አስመራ በዚያን ጊዜ በወታደር የተከበበች ነበረች፡፡ የሚወጣና የሚገባ የለም፡፡ ግን አንዳንድ የውስጥ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ያኔ የሕወሓት አባል ነበርን፡፡ ከኤርትራ ነፃ አውጭ ታጋዮች ጋር ግንኙነት ነበረን፡፡ ያኔ የደርግ አፋኞች ነበሩ፡፡ ሰው እየገደሉ መጣል ነው፡፡ በወቅቱ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው የነበሩት የትግራይ ተወላጆች ነበሩ፡፡ ሻዕቢያዎች እኔን ለማስወጣት ሁለት ሦስት ጊዜ ሙከራ አደረጉና ነገሮች ረገብ ሲሉ ይተውታል፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን መውጣቴ ግድ እንደሆነ ተነገረኝ፡፡ ለመውጣት ደግሞ የተፈጠረው ዘዴ ከገጠር ወደ ከተማ አትክልት የሚያመላልስ ጋሪ ነበርና ከእነርሱ ጋር የምሠራ መስዬ ነው የወጣሁት፡፡ እዚህ ላይ እስካሁን መልስ ያላገኘሁለት ነገር አለ፡፡ በዚያ ሁኔታ ስወጣ ጠባቂዎቹ አውቀው ወይስ ሳያውቁ ነው ያሳለፉኝ? ለሚለው ጥያቄ መልስ አላገኘሁም፡፡ ምክንያቱም ይፈትሻሉ፡፡ ለእኔ የተነገረኝ ግን ዝም ብለህ ጋሪው ላይ ተኛ ተብዬ ነው፡፡ ፍተሻው ላይ ስንደርስ ጠባቂዎቹ እየወሰዱኝ ያሉትን ሰዎች ያ ሰውዬ ማነው ብለው ጠየቁ፡፡ እነሱም ‹‹ወንድማችን ይሰክራል ይጠጣል›› ብለው ሲነግሩዋቸው እለፉ አሉን፡፡ ይህ እንግዲህ ኮድ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ እንጃ፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ወደ ሱዳን ለመውጣት ፍላጐት ነበረዎት?

አቶ ዳዊት፡- አዎ! የሕይወት ጉዳይ ነው…አፋኞች ነበሩ፡፡ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር፡፡ መውጣቴ ግድ ነበር፡፡ የትግራይ እንቅስቃሴ እየተጋጋለ የመጣበት ወቅት ስለነበር ቀለበት ውስጥ ገብተናል፡፡ ብዙ ታሪክ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- የትግሉ ተሳታፊ ነበሩ? አክቲቭ ነበሩ?

አቶ ዳዊት፡- በአጭሩ ነበርኩበት፤ በተሳትፎዬ ጉዳይ አክቲቭ ነህ አይደለህም ለሚለው መለኪያውን አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ሱዳን ከገቡ በኋላ ምን አደረጉ? ከዚህስ ሲነሱ ሱዳን ከገቡ በኋላ ለመሥራት አስበውት የነበረ ነገር አለ?

አቶ ዳዊት፡- በጣም የሚገርመኝና እግዚአብሔርን የማመሰግንው ከመጀመሪያው ጀምሮ ለሚሰጠኝ ዕድል ነው፡፡ ብዙ አጋጣሚዎች አሉኝ፡፡ ከሞት የተረፍኩበት ጊዜ ብዙ ነበር፡፡ ደግነቱ ከአስመራ እንደወጣሁ ጉዞዬ ብዙም ችግር አልነበረውም፡፡ ካርቱም ገባሁ፣ እስከዚያ በሕይወት መቆየቴም ዕድል ነው፡፡ ካርቱም ሕወሓት ጽሕፈት ቤት ተወሰድኩ፡፡ እዚያ እያለሁ ከአንድ ዘመዴ ጋር ተገናኘን፡፡ የእሷ ባልና በሱዳን የዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ አምባሳደር ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ እሷም የት መሄድ ትፈልጋለህ ስትለኝ ከዚህ አገር መውጣት እፈልጋለሁ አልኳት፡፡ የመጀመሪያ ዓላማዬ አሜሪካ መሄድና መማር ነበር፡፡ እሷ ደግሞ አቡዳቢ ልላክህ ወይ አለችኝ፡፡ ስለአገሩ ባላውቅም እሺ አልኳት፡፡

ፓስፖርት አልነበረኝም፡፡ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ተሠርቶ ተሰጠኝ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ አቡዳቢ ገባሁ፡፡ ይህም ዕድል ነው፡፡ ወደአቡዳቢ ስጓዝ አጠገቤ የነበረ ሱዳናዊ የት ነው የምታርፈው ሲለኝ እንግዳ ስለሆንኩ ሆቴል አርፋለሁ አልኩት፡፡ አሁን ጨለማ ስለሆነ ቤት ልውሰደህ ከዚያ ነገ የማውቃቸው ኤርትራውያን ስላሉ እነሱን አገናኝኃለሁ አለኝ፡፡ እሺ ብዬው በማግስቱ አንድ ኤርትራዊ ቤት ወሰደኝ፡፡ ልጆች ካላት ኤርትራዊት ጋር አገናኘንና ባሏን መጠበቅ ጀመርን፡፡ ባሏ ሥራ ነበር፡፡ ስሙን ሰምቻለሁ፡፡ መጣ፡፡ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ፤ ሰውዬው አብሮ አደጌና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብረን የተማርን ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህ በሆነ በሦስተኛ ሳምንቱ አንድ ጋዜጣ ላይ አቡዳቢ ናሽናል ኦይል ካምፓኒ የሚባል በጋዜጣ የሥራ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበርና ለመወዳደር ሄድኩ፡፡ ብዙ ተፈታኞች ቢኖሩም ከሚፈልጉት ሁለት ሰዎች አንዱ ሆኜ ተቀጠርኩ፡፡ እንግዲህ እየው በጥቂት ወራት ሁሉም ነገር ተሳካልኝ፡፡ ከዚህ የበለጠ ምን ዕድል አለ?

ሪፖርተር፡- ወደዋናው ጥያቄዬ ልመልስዎ ወደ ቢዝነስ ዓለም እንዴት ገቡ?

አቶ ዳዊት፡- እዚያ እያለሁ ሁሉም የሚያወራው ስለ ቢዝነስ ነው፡፡ ከድብቅ ስሜቴ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ አቡዳቢ ያሉት ኤርትራውያንና ጥቂት ኢትዮጵያውያን ተቀጥረው ነበር የሚሠሩት፡፡ በዚህ መሀል ትልቅ ዕድል የገጠመኝ በተቀጠርኩበት ኩባንያ የምሠራው በሽፍት መሆኑ ነው፡፡ 24 ሰዓት የሚሠራ ነው፡፡ ግን ሁለት ቀናት ብሠራ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ዕረፍት ነኝ፡፡ ግማሹን ቀን ብሠራ ግማሽ ቀን ዕረፍት ነኝ፡፡ ያኔ በዚህ አጋጣሚ ሁለት የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በትርፍ ጊዜዬ የመሥራት ዕድል አገኘሁ፡፡ አንደኛው የኢንሹራንስ ሌላው ደግሞ የፋይናንስ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያ የምሥራው ሥራ ደግሞ ሌላ መንገድ ፈጠረ፡፡ አንዱ ሥራዬ ብድር ለመስጠት ተበዳሪውን ማጥናት የሚል ነው፡፡ ለዚሁ ሥራ ወደተለያዩ ድርጅቶችና ሱቆች ሄጄ ባለቤቶቹን የሚያስፈልጉ ጥያቄዎችን ጠይቄ ሪፖርት ማቅረብ ነው፡፡ ብዙዎቹ ምንም ዓይነት ትምህርት የሌላቸው ናቸው፡፡ የፓኪስታንና የህንድ ዜጐች ይበዙባቸዋል፡፡

ግን ካፒታላችሁ ምን ያህል ነው ስትላቸው መልሳቸው ያስደነግጣል፡፡ እንዴት ጀመራችሁት ስላቸው ከጓደኛዬ የተወሰነች ተበድሬ እኔ ጋ ያለችውን ጨምሬ ነው ሥራ የጀመርኩት ይላሉ፡፡ የሚያገላብጡት ካፒታል ግን በሚሊዮኖች ነው፡፡ ይኼኔ ነው ራሴን መጠየቅ የጀመርኩት፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ከሠሩ እኔስ የማልሠራበት ምክንያት ምንድነው ብዬ ተነሳሁ፡፡ በግሌ የምሠራውን ሥራ ሳስብ አንድ የ‹‹ሜንቴናንስ›› ሥራ ታሰበኝ፡፡ በዚህ ሥራ መሥራት ቀላል ሆኖ አገኘሁት፡፡ ግን በራሴ ፈቃድ ማውጣት አልችልም፡፡ ኩባንያ ውስጥ እየሠራሁ ሌላ ፈቃድ ማውጣት ስለማልችል ነው፡፡

በዚህ መሀል በጋዜጣ ላይ የሚሸጥ ‹‹ሜንቴናንስ›› ኩባንያ አየሁ፡፡ ሻጩን አገኘሁትና ተስማማን፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቢዝነሱ ከየት ይመጣል ለሚለው ጉዳይ መልስ ማግኘት ነበረብኝ፡፡ ይኼኔ አንድ ነገር አሰብኩ፡፡ እኔ የምሠራበት ኩባንያ ሠራተኞቹን የሚያኖርበት ብዙ ፎቆች አሉት፡፡ ለእነዚህ ፎቆች በየዓመቱ ጨረታ እያወጣ ለአንድ ዓመት ኮንትራት እየሰጠ ያሳድሳል፡፡ እንግዲህ አንድ ነገር መፍጠር አለብኝ ብዬ የኩባንያችንን የቢዝነስ ኃላፊ አውቀዋለሁና በጣም ለትልቅ ጉዳይ ዕርዳታውን እንደምፈልግ አጠንክሬ ነግሬው ቀጠርኩትና ተገናኘን፡፡ ደንግጦ ነበር፡፡ ሳገኘውም መጀመሪያ እንቢ እንዳትለኝ አልኩት፡፡ ያሰብኩትን ነገርኩት፡፡ ከአንድ ‹‹ሜንቴናንስ›› ኩባንያ ጋር ተስማምቻለሁና ከአንተ የምፈልገው ኮንትራት እንድትሰጠኝ ብቻ ነው አልኩት፡፡ ደንግጦ ከእኛ ጋር እየሠራህ የኩባንያውን ሥራ እንዴት እሰጥሃለሁ አለኝ፡፡ የጥቅም ግጭት ይፈጥራል አለኝ፡፡ ሚስጥሩ በእኔና በአንተ ይቅር አልኩት፡፡ ሚስጥሩን ከጠበቅህ ብሎ ፈቀደልኝና ሥራውን አገኘሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቀም ያለ ገንዘብ አገኘሁ ያልኩት ያኔ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ ሲቀጠሩ የመጀመሪያ ደመወዝዎ ስንት ነበር? የኮንትራት ሥራውንስ ሠርተው ምን ያህል አገኙ?

አቶ ዳዊት፡- የመጀመሪያ ደመወዜ 3,500 ድርሃም ነበር፡፡ ወደ አንድ ሺሕ ዶላር አካባቢ ማለት ነው፡፡ በየዓመቱ ግን እያደገ መጥቶ ደመወዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ የኦቨር ታይም ገቢም ነበረኝ፡፡ ከኮንትራቱ ሥራ የተገኘው ብዙ ነበር፡፡ ይህንን ያህል ልልህ አልችልም፡፡ በዚያን ወቅት ነበር ወርቅ፣ የአልማዝ ሰዓት፣ የመሳሰሉትንና ጀልባ ጭምር የገዛሁት፡፡ ይህ ከ25 ዓመት በፊት ነው፡፡ ወደ አራት ዓመት አካባቢ እንዲህ እየሠራሁ ከሦስት አራት ቦታ ገቢ እያገኘሁ ቆየሁ፡፡ ሦስት አራት ሥራ እየሠራሁ አሥር ዓመት ሞላኝ ማለት ነው፡፡ በአሥረኛ ዓመቴ እሠራባቸው ከነበሩት ኩባንያዎች በፈቃዴ ለቀቅኩና የራሴን ኤጀንሲ አቋቁሜ ከአሜሪካን ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር ሦስት ዓመት ሠራሁ፡፡ በዚህ ሥራዬ ብዙ ሽያጭ ሠራሁ፡፡ ብዙ ሽልማቶችም አገኘሁ፡፡ ኑሮዬና ገቢዬ ሲያድግ አሜሪካን ረሳሁ፡፡ እስከመጨረሻው እዚያ ለመቆየት ወሰንኩ፡፡ ወደ አገሬ እመጣለሁ ብዬ ወጣሁ፡፡ የመጀመሪያውን የግል አየር መንገድ [ጐሽ ኤርዌይስ] መሠረትኩ፡፡ ቆይቶ ግን ሥራውን እንዳልቀጥል እንቅፋቶች ተፈጠሩ፡፡ በዚያን ወቅት ሥራውን ትቼ አገሬ እሄዳለሁ ስላቸው አላመኑኝም፡፡ ሦስት ዓመት ጠብቀውኝ ነበር፡፡ ይህን ያህል ገቢ እያገኘህ እንዴት ትለቃለህ አሉኝ፡፡ እዚህ ኢትዮ ግሎባል የሚባል ኩባንያም አቋቁሜ ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ዱባይ ተዛወርኩ፡፡ ሌሎች ሥራዎችም ሠራሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በጐሽ ኤርዌይስ ምን ያህል ከስረዋል?

አቶ ዳዊት፡- ይህንን ያህል ከሰርኩ ማለቱ ምናልባት ብዙ ላይጠቅም ይችላል፡፡ መገመቱ የሚሻል መሰለኝ፡፡ ምክንያቱም ለሦስት ፓይለቶችና ለአምስት ግራውንድ ቴክኒሻኖች ለዓመት ያለሥራ ደመወዝ ከፍለናል፡፡ አውሮፕላኑ የቆመበትንም ኪራይ እየከፈልን ነበር፡፡ ሌሎች ወጪዎችም አሉ፡፡ ዋናው ኪሳራ ግን አውሮፕላን ሲቆም የሚያመጣው ጣጣ ነው፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ ላንዲንግ ጊር የሚባለውን መቀየር ነበረብን፡፡ ምክንያቱም ዝም ብሎ ስለሚቆም መሥራት ያቆማል፡፡ ስለዚህ ይህንን ወጪ መገመት እንጂ ይህንን ያህል ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ዋናው ነገር ግን ጐሽ ኤርዌይስን መመሥረቴ ሌላ ቢዝነስ ለመክፈት መንገድ ከፈተልኝ፡፡ የእኛ አየር ኃይል የተለያዩ የመለዋወጫ ዕቃዎች ይፈልግ ነበርና እነዚህን ዕቃዎች ለማቅረብ ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ ከመለዋወጫ ዕቃ አቅራቢዎች ጋር ግንኙነት ፈጠርን፡፡ መለዋወጫዎቹ ከሁለት የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ናቸው፡፡ አንደኛው የምዕራባውያን ምርቶች ናቸው፡፡ ሌላው MI 17፣ MI 24… የሚባሉ የሩሲያ ሔሊኮፕተሮች ናቸው፡፡ በዚሁ መሠረት ለተወሰነ ጊዜ አየር ኃይሉ የሚፈልጋቸውን የመለዋወጫ ዕቃዎች ስናቀርብ ቆየን፡፡ ይህ ሥራ ደግሞ ከመለዋወጫ አምራቾች፣ እንዲሁም ከሔሊኮፕተርና አውሮፕላን አምራቾቹ ጋር እንድገናኝ አደረገኝ፡፡ በዚሁ መሠረት አምራቾቹን ወክዬ የመሥራት ዕድል አጋጠመኝ፡፡ ሥራው በመለዋወጫ ዕቃዎች ነበር የተጀመረው፡፡ ከዚያም ሔሊኮፕተርና አውሮፕላን ወደማስተዋወቅ ተሸጋገረ፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ወኪል ሆነው ይሠሩላቸው የነበሩ የሔሊኮፕተርና የአውሮፕላን አምራቾች የየት አገር ኩባንያዎች ናቸው? እነዚህን ምርቶች እንዴት ለማሻሻጥ ቻላችሁ?

አቶ ዳዊት፡- አንደኛው የአሜሪካ ሴስና የሚባለው ኩባንያ ነው፡፡ ሁለተኛው ሔሊኮፕተሮችን በተመለከተ ደግሞ እንሠራ የነበረው ከሩሲያ ኩባንያዎች ጋር ነው፡፡ በተለይ የሔሊኮፕተሩን ሥራ በጀመርን በጥቂት ጊዜ ልዩነት አጋጣሚ ሆኖ አንድ የአፍሪካ አገር የተለያዩ ሔሊኮፕተሮችን ይፈልግ ስለነበር፣ ይህንኑ ለማቅረብ እጅግ በጣም ከባድና ውስብስብ ሁኔታዎችን አልፈን ሸጥን፡፡ ሥራው በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህንን ሽያጭ ለማጠናቀቅ ከመጀመሪያው ድርድር እስከ ርክክቡ ድረስ ወደ አራት ዓመት ፈጀብኝ፡፡ ይህ ትልቅ ሥራ ወደተግባር ከመለወጡ ቀደም ብሎ የተፈጠረ አጋጣሚ ነበር፡፡ ይኸውም የሮተሪ ክለብ አባል ነኝና ወላጅ ያጡ ልጆችን በተለይ በኤችአይቪ ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች ዕርዳታ ለማሰባሰብ ፕሮግራም ነበር፡፡ በአገራችን በዚያን ወቅት መንግሥት ስለኤችአይቪ ብዙም አይልም ነበር፡፡ መድኃኒትን በሚመለከት የዓለም ባንክ የ500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እሰጣለሁ ብሎ ስለነበር አጋጣሚውን በመጠቀም በቀጥታ ወደ መድኃኒት አቅራቢነት ተሸጋገርኩኝ፡፡ ለዚህም ኩባንያ አቋቋምኩኝ ብዙ ሥራ ሠራን፡፡ ከዚህ አንፃር የቢዝነስ ሥራን እንዴት አሰብከው ላልከው እገባለሁ ብዬ አይደለም፣ ከወላጅ የወረስኩትም ነገር የለም፡፡ በውስጤ የነበረው ነፃ የመሆን ስሜትና ምናልባት በሄድኩበት አገር ያጋጠመኝ ሁኔታ ነው ወደ ቢዝነስ የወሰደኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በምን ዓይነት ሥራ ላይ ነዎት?

አቶ ዳዊት፡- አንድ ነገር ልንገርህ በእንዲህ ዓይነት ቢዝነስ ተሰማራሁ ማለት በቢዝነስ ዓለም አይቻልም፡፡ ለምን ካልከኝም ነገ የሚመጣውን አላውቅም፡፡ ትናንትና ሥሠራ የነበረው ሥራ ዛሬ ላይሆን ይችላል፡፡ ዛሬ የምሠራው ነገ ላይሆን ይችላል፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልህ እኔ እንኳን ስንት ሥራ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ አሁን ባለው ደረጃ እዚህ እየሠራሁ ያለሁት የሜዲካል አቅርቦት ነው፡፡ ይህ ሥራ ቀጣይ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው የተለያዩ ‹‹አዶ›› (ብዙ ጊዜ ሳታባክን የሚሠሩ) ቢዝነሶች አሉ፡፡ አጋጣሚው ተገኝቶ የሚገባባቸው ቢዝነሶች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ዳዊት፡- ጨረታ ሊሆን ይችላል፡፡ ሔሊኮፕተሮችን በተመለከተ ደግሞ በየወሩ በስድስት ወሩ የሚመጣ ቢዝነስ አይደለም፡፡ ‹‹አዶ›› ብለን የምንጠራው አንዱ እሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ግለሰብ ሳይሆን መንግሥት ነው የሚገዛው፡፡ መንግሥት ሲገዛ ደግሞ በሁለት ዓመት አንዴ ሊገዛ ይችላል፡፡ ሲገዛ ግን ከበድ ያለ ቢዝነስ ነው የሚሆነው፡፡ በአንድና በሁለት ቀን የምትጨርሰው ቢዝነስም ላይሆን ይችላል፡፡ ቅድም እንዳልኩህ እንዳለፈው ጊዜ አራት ዓመት አይፍጅ እንጂ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ በዱባይ ያለው ሥራዎ አሁንም በመካሄድ ላይ ነው? ኩባንያዎቹ ሥራ እየሠሩ ነው? ስንት ናቸው?

አቶ ዳዊት፡- ዱባይ ያሉት ሁለት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ አንደኛው ስካይ ቦርድ ቴክኖሎጂ ይባላል፡፡ ሁለተኛው ሜዲካል ፋርማ ብለን የምንጠራው ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚሠራ ነው፡፡ ዱባይ ያለው ቢሮ የአፍሪካ ብቸኛ ወኪል ነው፡፡ በተለይ ለሁለት ዓይነት ምርቶችን በብቸኝነት እንሠራለን፡፡ ከተለያዩ የመድኃኒት አምራቾች ጋር ተዋውለን በኤጀንትነት እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ያለው እንደ ቅርንጫፍ የሚታይ ነው ማለት ነው?

አቶ ዳዊት፡- እንደ ቅርንጫፍ ነው የሚታየው፡፡ ኬንያም አለ ወደሌሎች የአፍሪካ አገሮችም እየተስፋፋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በዓመት የሚያገላብጡት ካፒታል ምን ያህል ይሆናል?

አቶ ዳዊት፡- በሁለት መንገድ ይህንን ጉዳይ ባልመልሰው ደስ ይለኛል፡፡ ቅድም እንዳልኩህ አጋጣሚ ቢዝነሶች አሉ፡፡ በሕይወት ዘመን አንዴ ብቻ ሊሆኑ የሚችሉ ቢዝነሶች አሉ፡፡ ዓመታዊ መገላበጡ ይህንን ያህል ነው ልትል የምትችለው ዓይነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ፋብሪካ ቢሆን በሙሉ አቅሙ ይህንን ያህል ቢያመርት ይህንን ይህል ሊገኝ ይችላል ሊባል ይችላል፡፡ እንደኛ ዓይነት ቢዝነስ ግን እንዲህ ልትለው አትችልም፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን አሠራራችንም ትንሽ ለየት ይላል፡፡

እዚህም እዚያም የምንዘል አይደለንም፡፡ በትኩረት ነው የምንሠራው፡፡ ሥሠራ ደግሞ እርግጠኛ የምሆንበትን ነገር ነው፡፡ ሁለተኛ ገንዘብ አይደለም የምመለከተው፡፡ ሥራውንና ውጤቱን ነው፡፡ አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ አፍሪካ ኤንድ አስተርን የሚባል ኩባንያ ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ውስጥ አለ፡፡ ኩባንያው ለአፍሪካና ለመካከለኛው ምሥራቅ መጠጦች የሚሸጥ ነው፡፡ አውቃቸው ስለነበር የጆኒ ዎከር ውስኪ ኤጀንትነት እንስጥህና ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮሞት አድርግልን አሉ፡፡ እኔ ደግሞ አይሆንም አልኳቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ዳዊት፡- ምክንያቱም ከእኔ መርህ ጋር ስለማይሄድ ነው፡፡ መጠጥ ሸጬ፣ ውስኪ ሸጬ ሀብታም መሆን አልፈልግም፡፡ ይህንን እንደ አንድ ምሳሌ ነው የምነግርህ፡፡ ሌላው ጀባል አሊ የሚባል የሲጋራ ፋብሪካም ሮዝማንን በተመሳሳይ መንገድ እንድሠራላቸው ጠይቀውኝ ነበር፡፡ ለዚህም የሰጠሁት መልስ አይሆንም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውስኪ አከፋፋይ አልሆንም ብለውኛል፡፡ አሁን ደግሞ የራያ ቢራ ዋነኛ ባለድርሻ መሆንዎ ይታወቃልና አሁን ከጠቀሱልኝ አመለካከት ጋር አይጋጭም?

አቶ ዳዊት፡- በጣም ትልቅ ልዩነት አለው፡፡ ውስኪ ብሸጥ ትርፉ የእኔ እንጂ ለሌሎች የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ገንዘብ ብቻ ማግኘት ነው የሚሆነው፡፡ የውስኪ ፋብሪካ ልናቋቁም ነውና አክሲዮን ግባ ብባል ምናልባት ላስብበት እችላለሁ፡፡ እንዲህ ስል የማየው ነገር አለ፡፡ ውስኪ እንዴት ነው የሚሠራው? ከምንድን ነው የሚሠራው? ለምን ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር ይችላል? የሚለው እንዳስብ ያደርገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ራያ ቢራ ጉዳይ እንግባ፡፡ የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበርን እንዴት ለመቀላቀል ቻሉ? በተለይም በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያዎች ታሪክ በግለሰብ ደረጃ ትልቁን አክሲዮን እስከመግዛት ደርሰዋልና ወደዚህ ውሳኔ የደረሱት እንዴት ነው?

አቶ ዳዊት፡- ወደ ራያ ቢራ ለመግባት ከማሰቤ በፊት ውጭ አገር ያከማቸሁት ገንዘብ አገር ውስጥ መዋል አለበት የሚል የጠነከረ አቋም ነበረኝ፡፡ ወደ አገር መምጣት አለበት፡፡ ወደ አገር መምጣት ካለበት በቅድሚያ የታየኝና ያሰብኩት ግብረ ሰናይ ሥራ መሥራትን ነበር፡፡ ለዚህም የሚሆን ፈቃድ አውጥቻለሁ፡፡ ወጣቱ ራሱን የሚያሻሽልበት፣ የሚማርበትና ራሱን ችሎ ለአገር የሚጠቅምበት አንድ ሥራ ልፍጠር የሚል ነበር፡፡ ከእዚህ አቋሜ አንፃር መቀሌ ላይ 80 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ አንድ ፕሮጀክት ሠርቼ አቀረብኩ፡፡ ነገር ግን በትግራይ ክልል ድክመት ወይም ቀና አለመሆን ፕሮጀክቱ መሬት ሳይዝ ቀረ፡፡

ወጣቱ ራሱን የሚያሻሽልበት፣ በትምህርት ዕውቀት የሚያገኝበት፣ በሌላ በኩል ቋንቋችንን፣ ባህላችንንና ታሪካችንን የሚመለከት ምርምር የሚካሄድበት ተቋም ነው፡፡ ይህንን ሁሉ አጣምሮ የሚይዝ ፕሮጀክት በመቅረጽ አቀረብኩ፡፡ የመቀሌው ፕሮጀክት ቤተ መጻሕፍት፣ የአይቲ ማዕከል፣ የቋንቋ ኢንስቲትዩትና የመሳሰሉትን በመክፈት ወጣቱ ከከረንቡላና ከመሳሰሉት ቦታዎች ወደዚህ እንዲመጣ ለማድረግ ነው፡፡ መቀሌን ብታይ ወጣቱ ጊዜውን የሚያጠፋበት ቦታ ውስን ነው፡፡ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፍበት ቦታ የለውም፡፡ ይህንን ክፍተት በማየት ነው ፕሮጀክቱን የቀረጽኩት፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ጊዜ ይሆነዋል? ፕሮጀክቱ ያልተሳካበት ምክንያት ምንድነው? ይህ የሆነውስ መቼ ነው?

አቶ ዳዊት፡- በጣም የሚገርም ነው፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ ይመለከታቸዋል ከተባሉት ጋር ሁሉ ተነጋግረናል፡፡ የፕሮጀክቱ ዝርዝር ሁኔታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሐሳቡም ተስማምው ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ የተቀረጸበትን ምክንያትም ከፕሮጀክቱ ፕሮፋይል ጋር ቀርቧል፡፡ እንግዲህ እዚያ ውስጥ ያልተመቻቸው ቃላት አሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቃላት ሲባል ግልጽ አይደለም?

አቶ ዳዊት፡- ቃላት ሲባል መነሻው ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ የፕሮጀክቱን ዓላማና አነሳስ ከፕሮጀክቱ ጋር አያያዤ ሰጥቻለሁ፡፡ ለምን እንዲህ ዓይነቱን ፕሮጀክት መሥራት እንደፈለግኩ ተቀምጧል፡፡ እንግዲህ አንተ ቤት ለመሥራት ከፈለግህ ለምንድነው ቤት የምትሠራው ብሎ ሰው ሲጠይቅህ መልሱ ከፀሐይና ከዝናብ ለመከላከል ትላለህ እንጂ ዝም ብለህ ቤት አትሠራም፡፡ ላትገባበትና ላትኖርበት ቤት አትሠራም፡፡ ይህንንም ፕሮጀክት ሥሠራ ዓላማው መገለጽ ነበረበት፡፡ እውነቱን ነው ያስቀመጥኩት፡፡ ለማንም ጐንበስ ብዬ አላውቅም፡፡ የራሴ እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ነገሩን ግልጽ ያድርጉልኝ፡፡ የፕሮጀክቱ ተግባራዊ አለመሆን ምክንያቱ ቦታ በመከልከል ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

አቶ ዳዊት፡- የሆነውን ልንገርህ፡፡ ለፕሮጀክቱ ቦታ ምረጥ ተባለ፡፡ አምስት ስድስት ጊዜ ተመላልሼ ቦታውን መረጥኩ፡፡ ቦታው ነፃ መሆንና አለመሆኑ ይጠና ተባለ፡፡ ነፃ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ ከዚያ በኋላ እንፈራረም ተባልኩ፡፡ ለመፈራረም ሄድኩ፡፡ እዚህ ላይ በፕሮጀክቱ ፕሮፖዛል መሠረት ፕሮጀክቱ የሚመራው በቦርድ እንደሚሆን ገልጫለሁ፡፡

ምክንያቱም እንደ ግብረ ሰናይ ተቋም የሚታይ ነውና እኔ ከሞትኩም በኋላ ቢሆን ፕሮጀክቱ እንዲሸጥና እንዲለወጥ ስለማልፈልግ፣ በቦርድ ይተዳደር የሚል እምነት ስላለኝ ይህንኑ ፍላጐቴን የሚገልጽ አንቀጽ አካትቻለሁ፡፡ በቦርዱ የእኔ ወኪል የቦርድ ሊቀመንበር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ባለቤት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሌሎቹ የቦርድ አባላት ግን የአስተዳደሩ ባለሙያዎች ይሆናሉ የሚል ነው፡፡ ወደ ፊርማው ጉዳይ ልመልስህ፡፡ ለፊርማ ስሄድ ሁለት አንቀጾች ተለውጠው ወይም ተጨምረው ጠበቁኝ፡፡ አንዱ የእኔን ኃላፊነት የሚመለከተው ነው፡፡ አቶ ዳዊት ፕሮጀክቱን ሠርተው ሲጨርሱ ለክልሉ አስተዳደር ያስረክባሉ ይላል፡፡ ሁለተኛው ላይ ደግሞ አቶ ዳዊት ፕሮጀክቱን ሲጨርሱ አስተዳደሩ ይረከባል ይላል፡፡ እኔ ደግሞ ይህንን አንቀጽ ከየት አመጣችሁት አልኳቸው፡፡ እነሱም በቃ እንዲህ ነው መሆን ያለበት ሲሉኝ ሁለት ጥያቄዎች ጠየቅኳቸው፡፡

ይኸውም ፕሮጀክቱን ሠርቼ ብሰጥ እንዴት ልታስተዳድሩት ነው? በየትኛውስ አቅም? ለፕሮጀክቱ የሚለውን በጀትስ ከየት የሚመጣ ነው? ስንት መደባችሁ? መልስ አላገኘሁም፡፡ ስለዚህ ዓላማዬን ታውቃላችሁ፡፡ ተነጋግራችሁ ደውላችሁ ንገሩኝ ብዬ መጣሁ፡፡ጉዳዩን በተመለከተ በስልክም በግንባርም ሄጄ ጠየቅኩ፡፡ ምንም መልስ አጣሁ፡፡ የሚሰማኝን ተናገርኩ፡፡ እኔ ሀብቴን ላፍስ ባልኩ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከገጠመኝ ለሌላ ለኢንቨስትመንት የመጣውንስ እንዴት ልታደርጉት ነው ብዬ በግልጽ ተናገርኩ፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ወደ ሌላ እወስዳለሁ ብዬ ተናገርኩ፡፡ ዓደዋ የምሠራው ሥራ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዓደዋ ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?

አቶ ዳዊት፡- የዓደዋ ፕሮጀክት እንቅስቃሴ ቆሟል፡፡ አንዴ በሙስና ይጣራ ይባላል፡፡ ቦታ አሰጣጡ ይታይ የሚል ነገርም አለ፡፡ ችግር አለበት እየተባለ ይገለባበጣል፡፡ ለሕዝብ የሚሠራ ሥራ ስለሆነ ነገሩ ቀላል አይሆንም፡፡ ምንም ቢሆን ግን እሠራዋለሁ፡፡ በነፃ ለምሠራው ሥራ ፈተናው በዛ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ራያ ቢራ እንዴት ገቡ አላብራሩልኝም?

አቶ ዳዊት፡- ቀደም ብዬ በመቀሌ፣ በዓደዋና በአክሱም ስለምሠራቸው ሥራዎች ያነሳሁልህ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ወደ ራያ ከመግባቴ በፊት እነዚህን ማዕከላት ለመገንባት ማቀዴን ለማስታወስ ነው፡፡ በመካከሉ ግን ከሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ሕዝቡን ትንሽ ለማንቀሳቀስና ሥራ ለመፍጠር የቢራ ፋብሪካ ትልቅ አንቀሳቃሽ ስለሆነ ይህ ቢደረግ የሚል ሐሳብ መጣ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይጠጣም ማለት አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ይህ ከታሰበ የታሰበውን ነገር መጨረስ ይኖርብናል፡፡ ትግራይን እንደምታውቀው የተጐዳ ሕዝብ ነው ያለው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የተጐዳው በሁለትና በሦስት ነገሮች ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ጉዳት አለ፡፡ በሌላ በኩል የጦር አውድማ ሆኖ የቆየ ቦታ ነው፡፡ ከቀድሞ ነገሥታት ጀምሮ ቦታው የጦርነት ቦታ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አስተዳደራዊ ችግር አለበት፡፡ ራያም ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው ሕዝብ ችግር የለበትም ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በቢራ ፋብሪካው ሥራ መፍጠር የምንችል ከሆነ እንግባበት ብዬ ገባሁ፡፡ ራያ ቢራን ስትመለከት ፈርጀ ብዙ ጥቅም የሚሰጥ ሥራ ይኖረዋል፡፡ አንደኛ የፋብሪካው ግንባታ ሒደት የሚፈጥረው የሥራ ዕድል አለ፡፡ ሁለተኛ የማከፋፈልና ብዙ ተያያዥ ሥራዎች አሉት፡፡ ገቢ ሲገኝ ሰዎች ቤት ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቢራ መመረቱን ብቻ አንይ፡፡ ሌላው ደግሞ ፋብሪካው የሚቋቋምበት አካባቢ ገብስ የሚበቅልበት ስለሆነ በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች የቢራ ገብስ አምርተው ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሦስተኛው የብቅል ፋብሪካም የማቋቋም ዕቅድ አለን፡፡ ይህ ደግሞ ለራያ ቢራ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ የጠርሙስ ፋብሪካም የመገንባት ዕቅድ አለና ይህ ሁሉ ብዙ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- መጀመሪያ 55 ሚሊዮን ብር ከዚያም ከዚህ በላይ የሚሆን አክሲዮን እየገዙ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃዎ ለብዙዎች አስገራሚ ሆኗል፡፡ በዚህን ያህል መጠን ለመግዛት ውሳኔ ላይ የደረሱበት የተለየ ምክንያት አለ?

አቶ ዳዊት፡- ይህንን ሁሉ ገንዘብ ለምን አስገባህ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ነገሮች ማለት ይቻላል፡፡ አንደኛው እንደ አጋጣሚ ሆኖ ገንዘቡ አለ፡፡ ገንዘቡን ደግሞ ተበድሬ ያመጣሁት አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ገንዘብ ተበድሬ አላውቅም፡፡ በመርህ ደረጃ ባንክ ሄዶ መበደርን አድርጌው አላውቅም፡፡ ለማንኛውም አነሰም በዛ ገንዘቡ አለ፡፡ ወደ 32 ዓመት ገደማ ያጠራቀምኩት ገንዘብ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ቁም ነገር ላይ መዋል አለበት፡፡ በዚህን ያህል ብር አክሲዮን ስገዛ ደግሞ በዶላር የተላለፈ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመሪያው የ55 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ግዥ በዶላር የተላለፈ ነው?

አቶ ዳዊት፡- አዎ! እንዲያውም የራያ ቢራ ጥንስስ ሲጀመር ለሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከውጭ በዶላር ነበር የሚከፈለው፡፡ የመጨረሻው የአክሲዮን ክፍያ ለራያ ሲገባ የተከፈለው በብር ቢሆንም ገንዘቡ የተላለፈው በዶላር ነው፡፡ ስለዚህ ክፍያው የተፈጸመው በዶላር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እኔ አዲስ አበባ ገንዘብ የለኝማ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የምሠራው ካለ ወጪያችንን ከሸፈነልን ጥሩ ነው፡፡ ወደ ሁለተኛው ነጥብ ስሄድ ደግሞ መጀመሪያ ቃል የገባሁትን መፈጸም አለብኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ቃል የተገባው ምንድነው?

አቶ ዳዊት፡- ያ ቃል ከሌተና ጄኔራል ፃድቃን ጋር ስንነጋገር አንዴ ከጀመርነው መጨረስ ይኖርብናል የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ ዳዊት ማነው? ምን ያህል አለው? የሚለውን የሚያውቁት ሦስት ወገኖች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም እኔ፣ ባንኬና እግዚአብሔር ብቻ!!

ሪፖርተር፡- እንዲያው አሁን ምን ያህል ሀብት አለዎት?

አቶ ዳዊት፡- አቤት … አቤት …. (አይሰማም እንደማለት)

ሪፖርተር፡- አቶ ዳዊት ምን ያህል አላቸው የሚለው ጥያቄ ያለምክንያት የሚነሳ አይደለም፡፡ አንድ ሰው 55 ሚሊዮን ብር በጥሬ ከፍሎ እንደገና 70 እና 80 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ አክሲዮን በአንድ ወር እከፍላለሁ ሲል ብዙዎችን ማስገረሙ አይቀርም፡፡

አቶ ዳዊት፡- ይኼ የለበስኩት ልብስ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪም እያለሁ የምለብሰው ልብስ ነው፡፡ ገንዘብ አለኝ ብዬ ሀብት አለኝ ብዬ ለማሳየት ሙከራ ያደረኩበት ጊዜ የለም፡፡ ሸራተን ጓደኞቼን ለማግኘት በሳምንት አንዴ መሄድ እችላለሁ፡፡ አንድ ጥግ እይዛለሁ፡፡ እዚያ ስቀመጥ ደግሞ ጓደኞቼን የማስቅበት ነገር አለ፡፡ አንድ ያስቀዳትን ብርጭቆ እያሽሞነሞነ ያቆያታል ይሉኛል፡፡

ሪፖርተር፡- መጠጥ አይጠጡም ማለት ነው?

አቶ ዳዊት፡- አልጠጣም፡፡ አልጠጣም ማለት ግን አልቀምስም ማለት አይደለም፡፡ ጓደኞቼን ብትጠይቅ አንድ ብርጭቆ ለመጠጣት ሰዓታት እወስዳለሁ፡፡ መኪኖች ይኖራሉ፡፡ አንድ አምስት ስድስት መርሰዲሶች ይኖራሉ፡፡ የምነዳው መርሰዲስ የቆየ ነው፡፡ እዩልኝ እወቁልኝ አልልም፡፡ ቃል ወደመጠበቅ ወዳልኩህ ልመለስ፡፡ ከጀመርነው መጨረስ አለብን የሚለው አቋሜ እንዳለ ሆኖ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ራያ ቢራ እንዳይቋቋም ታጥቀው የተነሱ ነበሩ፡፡ እነማናቸው የሚለውን ነገር ተወው፡፡ እስቲ ሲቋቋም እናያለን ብለው የፎከሩ ነበሩ፡፡ ይኼኔ ነው እንግዲህ እኔ ወገቤን ጠበቅ እንዳደርግ ያደረገኝ፡፡ እዚህ ላይ ማወቅ ያለብህ ራያ ቢራ ሲጀመር አምስት ሚሊዮን ብር ነበር ያዋጣሁት፡፡ የሰጠሁትም አስተዋጽኦ ብዬ ነው፡፡ ቃል በቃል ያልኩት ከዚህ ትርፍ አልፈልግም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአክሲዮን የማይታሰብ ትርፍ የማልወስድበት ይሁን እንደማለት ነው?

አቶ ዳዊት፡- ከማንኛውም ኢንቨስትመንት አሁን ካለውም ትርፍ ባላገኝ ግድ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ የቢዝነስ ሰው ትርፍ የማይኖረውን ሥራ ይሠራል ብሎ የሚያስብ የለም እኮ?

አቶ ዳዊት፡- የለም፡፡ ነገር ግን የእኔ ዓላማ አለው፡፡ ለዚያ አካባቢ ሥራ ከፈጠረና ሰዎች ትንሽ መንቀሳቀስ ከቻሉ፣ ከዚያ ልጆቻቸውን ማሳደግ ከቻሉ ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋለህ? ለእኔ ትርፍ ይኼ ነው፡፡ ገንዘብ ምን ያደርግልኛል? ገንዘብ ትርጉም ያለው ሥራ ላይ ካላዋልከው ምን ዋጋ አለው? ምናልባት እንዴት እንደምመገብ ብነግርህ ትደነግጥ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲያውም እዚህ ምሳ አልበላም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ዳዊት፡- ገንዘብ ለመቆጠብ (እንደ ጨዋታ) እዚህ ምሳ አልበላም ያልኩህ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከበላሁ ትንሽዬ አምባሻ ከቢሮዬ ታች ካለች ሱፐር ማርኬት አስመጥቼ ነው፡፡ (እንዲያውም ልጋብዛችሁ ብለው ዘወትር እበላዋለሁ ያሉትን አንባሻ አዘዙ) ይቺን አንባሻ እኔ፣ ጸሐፊዬና ጓደኛዬ ተካፍለን በማር ቀብተን እንበላለን፡፡ እኔ ይህን በልቼ እውላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ የሚያደርጉበት ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ዳዊት፡- አንደኛው ለምግብ ብዙም አልጣደፍም፡፡ እናም ዛሬ ግን በአጋጣሚ ወዳጄ ምሳ ካልበላህ ብሎ ለክብሩ ስል በልቻለሁ እንጂ፣ ሳምንቱን ሙሉ የትም አልወጣሁም፡፡ ልታይ ብዬ በየምሽቱ ሸራተን መሄድ አይመቸኝም፡፡ አሁንም ወደቀድሞ ጥያቄህ ልመለስ ገንዘቡ አለ ብዬሃለሁ፡፡ ሁለተኛው በትዕቢት ራያ ቢራ ሲቋቋም እናያለን ያሉና አፋቸውን ሞልተው የተነሱትን አፋቸውን ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩህ ከእኔ፣ ከባንክና ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም አያውቅም ያልኩህ ለዚህ ነው፡፡

በአምስት ሚሊዮን ብር ስጀምር ለትርፍ አልነበረም ያልኩህ ለዚህ ነው፡፡ ከአምስት ሚሊዮን ብር ስጀምር ብዙ ሰው በስሜት ሲነሳሳ ሳይ 10 አድርጌዋለሁ አልኩ፡፡ 10 ሚሊዮን ብር ለዳዊት ትልቅ ነገር ሆኖ የታያቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚሁ መንገድ ስሄድ የሚፈለገውን ገንዘብ ለመሙላት ቦርዱ ሲጨናነቅ አንድ ነገር ሹክ አልኳቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት ስብሰባም የራያ ቢራ ጉዞ እንደሚቀጥልና ግድ የላችሁም ብዬ አክሲዮኔን ወደ 20 ሚሊዮን ብር ከፍ አደርጋለሁ ብዬ ስናገር ብዙ ሰው ደንግጦ ነበር፡፡ ሌላውንም ያበረታታል ብዬ ነው ያደረግኩት፡፡ ዳዊት እንኳን 20 ሚሊዮን ብር ይቅርና አምስት ሚሊዮን ብር አይኖረውም ብለው የተጠራጠሩ አይጠፉም፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ተጋኖ ጭምር በጋዜጣ የወጣው፡፡ እኔ አልነበርኩም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ቢሮዎ ስገባ ‹‹ዳዊት ጐልድ›› የሚል ኩባንያ ያለዎት መሆኑን የሚያሳይ ማስታወቂያ አይቻለሁ፡፡ ወደ ወርቅ ሥራ እየገቡ ነው? ሌላ ቢዝነስ አለዎት? የሕይወት መርህዎ ምንድነው?

አቶ ዳዊት፡- በቢዝነስ ዓለምም ሆነ በሕይወት በአጠቃላይ አንዱ ከአንዱ የሚለየው፣ አንዱ ሲራመድ ግራ ቀኙን እያየ ነው፣ አንዳንዱ ሰማይ ሰማይ እያየ ይሄዳል፡፡ ግራ ቀኙን ረግጦ የሚሄድ አለ፡፡ ስለዚህ እኔም ከአባቴም ሆነ ከቤተሰብ የወረስኩት የለም፡፡ ቢዝነስ አልተማርኩም፡፡ ከቢሮ ወደ ቤት ነው የምሄደው፡፡ እንኳን አሁን ይቅርና በትዳር ላይ በነበርኩበት ጊዜ ቅዳሜ ከሰዓት ገብቼ እሑድ አልወጣም፡፡ ይህንን እንደ መርህ የማየው ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ምን ዓይነት ሥራ ውስጥ ትገባለህ ለሚለው ግን ገንዘብ አተርፋለሁ ብዬ አይደለም፡፡ የወርቁን እንዴት እንደጀመርኩ ልንገርህ፡፡ ዓደዋ ካለው ቤታችን አንድ ሁለት ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የወላጆቼ ቤተ ክርስቲያን ነበርና ወደዚያ ስንሄድ ወንዝ ዳር ሰዎች አየን፡፡ ምን እያደረጉ ነው ስል ወርቅ እየፈለጉ ነው ተባልኩ፡፡

እነሱ ዘንድ ሄጄ ከሰዓት በላይ ቆይቼ አዋራኋቸው፡፡ አበረታታኋቸው፡፡ ከዚያ ነገሩ ገረመኝ፡፡ እኛ እዚያ አድገን ያኔ እንዲህ ዓይነት ነገር አልነበረም፡፡ ይህንን ባየሁ በዓመቱ እንደገና ወላጆቼን ለማየት ወደ ዓደዋ ስሄድ እነዚያ ሰዎች አሉ፡፡ ከዚያ እንዲህ ከሆነና ዕድሉ ካለ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡ እኔ አቅም ካለኝ እዚያ ያለውን ሰው አሰባስቤ ይህንን የተቀበረ ሀብት ባወጣ እኔ ሳልሆን ሕዝቡ ይጠቀማል የሚል ነገር መጣብኝ፡፡ የወርቁን ኩባንያ ያቋቋምኩት ለዚህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ዳዊት፡- ጥናት ተደርጐ ሌሎች አካባቢዎችም ተገኝተው አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሟልተንና ሠርተፊኬት ወስደን የፍለጋ ሥራ እየሠራን ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች የቢዝነስ ሥራዎችስ?

አቶ ዳዊት፡- ሊኖሩ ይችላል፡፡ ለዝርዝሩ ጊዜ ስጠኝ፡፡ ግን አሉ፡፡ ከራያ ቢራ ጋርም የተያያዙ ሌሎች ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከዚህ ውጭ በዓደዋ፣ በአክሱምና በመሳሰሉት ቦታዎች የምሠራቸው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደፊት የሚንቀሳቀሱት ከራያ ቢራ በሚገኘው ትርፍ ነው፡፡ ትርፉ በሙሉ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚውል ነው፡፡ ለልጆቼ የማደርገው ነገር ካለ ራሳቸውን እስኪችሉ መርዳት ብቻ ነው፡፡ ተጧሪ መሆን የለባቸውም፡፡ በአባታቸው ንብረት ተጧሪ አይሆኑም፡፡

ይህንን በግልጽ ያስቀመጥኩትና ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ ወራሽ የለኝም፡፡ ያሰብኩትን ለማሳካት ዕድሜና ጤና ይስጠኝ፡፡ የእኔ ዕቅድ ግን ከራያ የሚገኘው ትርፍ በራሴ ወጪ የማሠራቸው ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል ነው፡፡ አንድ ጊዜ ትልቋ ልጄን አንድ ሚሊዮን ዶላር ልስጥሽ ወይስ ራስሽ ሠርተሽ ነው ሚሊየነር መሆን ነው የምትፈልጊው ስላት፣ ‹‹ኖኖ ራሴ ሠርቼ ነው መሆን የምፈልገው›› ብላኛለች፡፡ አሁን በኢንተርናሽናል ቢዝነስ ማኔጅመንት ማስተርሷን ይዛለች፡፡ አሁን ውጭ አገር አንድ ሱቅ ውስጥ ነው የምትሠራው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ደግሞ ቢዝነስ እንድታቋቁም ረዳታለሁ በቃ፡፡

ሪፖርተር፡- ገንዘቡ ውጭ ነው ያለው ሥራም እዚያ ነው፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ ለዚህ ካወጡ ሥራዎን በምን ሊሠሩ ነው?

አቶ ዳዊት፡- እግዚአብሔር አለ’ኮ!

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ሰዎች አቶ ዳዊት ይህንን ያህል ገንዘብ ከየት አገኘ ቢሉ ምን ይመልሳሉ?

አቶ ዳዊት፡- ቅድም ያልኩህን በላቸው፡፡ ሀብቱን የሚያውቁት ዳዊት፣ እግዚአብሔርና ባንኩ ብቻ ናቸው፡፡ ሰው በሒደት ቢያየው ያውቀው ነበር፡፡ ያለኝን ሁሉ መናገር አለብኝ? ያለኝ ሁሉ ግን እዚህ ነው የሚፈሰው፡፡

03161062
Today
Yesterday
This Month
Last Month
All days
2982
4118
86575
75600
3161062

Since April 1, 2014

Photo Gallery