You are here: HomeARTICLESበሶሻል ሚዲያ አማካኝነት የተመሰረተው የዲያስፖራው አክሲዬን እጣ ፈንታ ምንድን ነው? በሰለሞን ተካልኝ፣ ከጽናት ራዲዬ

በሶሻል ሚዲያ አማካኝነት የተመሰረተው የዲያስፖራው አክሲዬን እጣ ፈንታ ምንድን ነው? በሰለሞን ተካልኝ፣ ከጽናት ራዲዬ

Published in Articles
Rate this item
(1 Vote)

Ethiodemocracy April 4/2016 -  “ኩራት በኢትዮጵያ” አግሮ-ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ አ/ማ በዲያስፖራው ውስጥ አሁንም ያልበረደ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በጥቂት የዲያስፖራ አባላት አነሳሽነት ተመስርቶ ለፍሬ በቃ ሲባል፣ አደገ ተመነደገ፣ ወፌ ቆመች እየተባለለት ገና ጠንክሮ መራመድ ሳይጀምር የውዝግብ ርእስ የሆነው ማህበር የብዙዎች ትኩረት ሆኗል፡፡
ለመሆኑ ማህበሩ፣ በነማን እና እንዴት ተመሰረተ? የውዝግቡ መነሻስ ምንድን ነው? ከዚህ አይነቱ አካሄድስ ሌላው ዲያስፖራ ምን ሊማር ይችላል? የሚለውን ጥቂት መረጃ እናካፍላችኋለን፡፡
አድማጮቼ ሁላችሁም እንደምታውቁት ዲያስፖራው በሰው ሃገር ጥሮ ግሮ ያጠራቀማትን ሃብት በኢንቨስትመንት ሃገሩ ላይ እንዲያፈስ እና እርሱም ተጠቅሞ ወገኖቹንም በመጥቀም ሃገሩንም በማሳደግ ብዙ እንዲያተርፍ ሁላችንም የምንሰራለት አላማ ነው፡፡
በተደጋጋሚ እንደምንለውም በአለም ላይ የዲያስፖራዎቻቸውን አቅም በመጠቀም ብቻ እድገታቸውን እያፋጠኑ ሃገራትን ተሞክሮ ከዚህ በፊትም በዝግጅታችን ደጋግመን አቅርበነዋል፡፡
ከዚህ አንጻር በሃገራችን እንኩራ ብለው ስያሜያቸውንም “ኩራት በኢትዬጵያ” ብለው በፓልቶክ አማካኝነት የተሰባሰቡት ኢትዬጵያዊያን ጅምራቸው የሚያስቀና ሆኖ ወደ መደራጀት ገብተዋል፡፡
እነዚሁ ለልማት የተጠራሩ ወገኖቻችን ቁጥራቸው ወደ 200 የሚጠጋ፣ ለኢንቨስትመንት ያስመዘገቡት ካፒታልም ከ20 ሚሊዬን ብር በላይ እንደሆነ ያገኜነው መረጃ ያሳያል፡፡ 5.5 ሚሊዬን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ መደራጀት የገባው ኩራት በኢትዬጵያ አስተባባሪ አባላት እንዳሉት የተገለጸ ቢሆንም ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው እንዲሉ የባለቤትነት እና የመስራችንት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ግን በአባላቱ መካከል ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡
በተለይም ደግሞ ብዙዎቹ መስራች አባላቱ የሚኖሩት በውጭ በመሆኑ እና ጉዳዬን በቅርበት በሃገር ቤት መከታተል አለመቻላቸው ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል፡፡
የአንድ አክሲዬን ዋጋ 5ሺህ የኢትዬጵያ ብር ሲሆን 200 አባላቱ የመስራችነት ባለቤትነት መብት አለን ሲሉ ጥያቄ ቢያቀርቡም ሂደቱን ሲያስተባብሩ የነበሩ ወደ አስራ አንድ ሰዎች ግን ይህንን ማረጋገጥ አልቻሉም ሲል ሰንደቅ ጋዜጣ የሚመለከታቸውን አነጋግሮ አስነብቧል፡፡
እዚህ ላይ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ዋና መስርያቤት የሰነዶች ማረጋገጥ እና መመዝገብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ምናሴ ጌታሁን እንደገለጹት በመስራችነት የተመዘገቡት 11 ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ታዲያ ቀሪዎቹ የት ገቡ? የሚለውን ጥያቄ የብዙዎች ነው፡፡ ምንም እንኳን ከመስራቾቹ መካከል ለሰንደቅ መረጃ ሰጡት እንድ ሰው የመስራችነት መብቱ የሁሉም ነው ቢሉም የመስራችንት ሰርተፍኬት ለጠየቁ ዲያስፖራዎች ግን ምላሽ አልሰጡም በሚል ወቀሳ ይነሳባቸዋል፡፡
እንግዲህ የኩራት ጉዳይ በዚህ መልኩ እየታመሰ መስራች ነን የሚሉትም ችግር የለም አሁንም የናንተው ነው ቢሉም መተማመን ላይ ግን መድረስ አልተቻለም፡፡
ከዚህ አልፎም ቅድሚያ የተከፈለውን ገንዘብ በተለያዬ አግባብ ለማንቀሳቀስ የሞከሩ የተመዘገቡ መስራቾች አሉመባሉ የበዙትን ቀሪዎቹን ስጋት ላይ ጥሏቸዋል፡፡
እኛም ጉዳዬን በቅርበት ለማጣራት እንደሞከርነው እና አንዳንዶቹ አክሲዬን ባለድርሻወችን ቅሬታቸውን እንደገለጹልን ሂደቱ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬን ያጫረ ነው፡፡
ምንም እንኳን ገንዘቡ አሁንም በባንክ ውስጥ ሆኖ ማንም የፈለገ የሚያንቀሳቅሰው አለመሆኑ ጥሩ ቢሆንም የአክሲዬኑ ቀጣይ ጉዞ ምን ይሆናል? በዚህ ሂደትስ ተጨማሪ ገንዘብ በማዋጣት ወደ ታለመው ስራ እንዴት መግባት ይቻላል? የሚሉና ሌሎችም ብዙ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡
እንግዲህ ከዚህ ጋር በተያያዘ መነሳት ያለበት ዋናው ነጥብ ይህን እና ይህን መሰል ለኢንቨስትመንት የመሰባሰብ እንቅስቃሴ በዲያስፖራው መካከል ያለውን መተማመን እንዳያጠፋው ምን መደረግ አለበት? እንዲህ ያለው ነገር እንዳይከሰትስ ጥንቃቄው ምንድን ነው? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡
በዋናነትም ብዙ አቅም የሌላቸው እና በግላቸው ብቻቸውን ወደ ኢንቨስትመንት መሰማራት የማይችሉ ዲያስፖራዎች ተደራጅቶ የማልማትን አሰራር እንዳይከተሉ እንቅፋት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አንጻር የአንድ ሃገር ዜጎችም ሆኑ ሌሎች ተጨምረውበት አክሲዬን በመሸጥ አንድ የኢንቨስትመንስ ስራ ላይ ተሰማርቶ መስራት የተለመደ አለም አቀፍ አሰራር መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ጠቃሚ ነው፡፡
ስለዚህ እንዲህ ያለውን አለም አቀፍ ተሞክሮ ለመጠቀም በሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እድሎች አሉ፡፡ የህግ ማእቀፎች፣ አሰራሮች እና ትብብሮች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዲያስፖራው ማድረግ የሚገባው ጉዳይ አክሲዬኖቹ ምን ያህል ህጋዊ አሰራርን ተከትለው የሚንቀሳቀሱ ናቸው? የሚለውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ድርጅቶቹ ህጋዊ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በገንዘብ ዝውውር እና በአባልነት ጥያቄ ላይም ተሳታፊው ግለሰብ ወይም ድርጅት ተጠቃሚነቱ በህግ የሚረጋገጥለት እስከምን ድረስ ነው የሚለውንም መመለስ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ አንጻር ኑና በኢንቨስትመንት እናስተባብራችሁ የሚሉትን ግለሰቦች ፕሮፋይል ከማወቅ ጀምሮ በህግ አግባብ የተጓደለ ነገር ሲኖርም እስከምን ድረስ እጠይቃለሁ የሚለውን ማሰብም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
በ1990ዎቹ መንግስትን በሃይል ለማውረድ በዲያስፖራው ውስጥ ቀንደኛ አንቀሳቃሽ ሆነው ገንዘብ ሲሰበስቡ እና ድንጋይ ሲያስወረውሩ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ለልማት እናስተባብራችሁ ሲሉንም እንዴት? እና ለምን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
እንዲህ አይነት ሰዎች ትክክለኛውን የልማት መስመር መርጠው በሃገራቸው ልማት ለመሳተፍ እና ለማልማት የሚከለክላቸው ባይኖርም ለማስተባባር ግን ብቁ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡
ለዚህም ነው ጥንቃቄ ያስፈልጋል የምለው፡፡ እንዲህ አይነቶቹ ከምስኪኑ ዲያስፖራ የቻሉትን ያህል ለመዝረፍ ብቻ ሳይሆን ከዘረፉም በኋላ ሌላው ነገ በኔ ብሎ ከልማቱ እንዲሸሽ ለማድረግ የሚሰሩ ናቸው፡፡
ይህንን ቀድሞ በማወቅና በመረዳት ደግሞ ዲያስፖራው ራሱ ጠያቂ እና ለጥቅሞቹ ታጋይ መሆን አለበት፡፡ በዲያስፖራው ውስጥ ሲፈጠሩም ስህተት ፈጣሪዎችን ዲያስፖራው በራሱ መታግል አለበት፡፡
እዚህ ላይ ሁላችንም መረዳት ያለብን ነገር በሃጋችንም ሆነ በራሳችን ግል ጉዳይ ላይ የሆነ ነገር ስናገኝ የሚሞቀን ትንሽ ችግር ሲፈጠር ደግሞ ደብሮን ቆፈን የሚይዘን መሆን የለብንም፡፡ አስቡት እንግዲህ ኢንቨስት ማድረግ ሲባል ፍላጎት ብቻውን ወደ ተጠቃሚነት አይወስድም፡፡ ካፒታል ማፍሰስ፣ የሰው ሃይል ማስተዳደር፣ መገንባት፣ ማምረት ወይም አገልግሎት መስጠት የሚሉ እልህ አስጨራሽ ተግባራት አሉት፡፡ ለነዚህ ተግባራዊነት የሚተጋ ሰው ደግሞ ገና ከጅምሩ ሚደክመው ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩም እነ እንትና እንደሚሉት ጉዳዬን መንግስት በማድረግ ብቻ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡
ከዚህ አንጻር የዚህ የተጠቀሰው ድርጅት አባላት በዋናነት ጥቅማቸው ወይም ብራቸው በሚገባ አሁንም በመንግስት እጅ ያለ ቢሆንም ከመሰል ውዝግቦች ለመዳን ግን አስቀድሞ ሂደቱን መመርመር ያስፈልጋል፡
በውስጣችን ያሉ ችግር ፈጣሪዎችም በራሳችን መፍታት እና ታግለን መጣል ካልቻልን ፌስ ቡክና ዬቱዬብ ላይ የሚፈታ የኛ ችግር የለም፡፡
በነገራችን ላይ ይህንን የሰሞኑን “የኩራት በሃገር” ውዝግብንም ለጥላቻ ፖለቲካቸው ፍጆታ እንማን በምን ሁኔታ ሲያሟሙቁት እንደሰነበቱ ሁላችሁም ታዝባችኋል፡፡
ምንም እንኳን ጉዳዬ ከመንግስት ጋር ወይም ከድርጅቱ ጋር የሚያገናኜው ነገር ባይኖርም፣ “ወያኔ ብራችሁን ዘረፈ፣ ድሮም አርፋችሁ እንድትቀመጡ ነግረናችሁ ነበር” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
እዚህ ላይ የተባለውን እንደተባለ ሳያላምጡ ለሚውጡት እንተወውና ሂደቱን በጥሞና ለተመለከተው ግን መንግስት በመስራችነት ያልተመዘገቡትን (ከ11ዱ ፈራሚዎች ውጭ ያሉትን ማለቴ ነው) 189 ዲያስፖራዎች ገንዘባቸውን ጠበቀላቸው ወይስ ወሰደባቸው ብሎ ማየት ይጠቅቃል፡፡
ሲባል የነበረውን አሉባልታ እዚህ ላይ ብናመጣው “ከአንቀሳቃሾቹ ውስጥ እንድ ሁለቱ ገንዘቡን ከልማት ባንክ አውጥተው ወደ ግል አካውንታቸው ሊያስገቡ ሲሉ ተከለከሉ” የሚል ወሬ በሰፊው ተናፍሷል፡፡
ታዲያ እንዲህ ከሆነ መንግስት በራሳቸው በአክሲዬኑ መስራቾች ህጋዊ እውቅና ያልተሰጣቸውን አባላት ገንዘብ ጠበቀ እና ከመቀማት አዳነ ነው መባል ያለበት ወይስ ቀማ ነው የሚባለው? እንግዲህ በቂም በቀል የተነሱት ፖለቲከኞች ነን ባዬች መንግስት ቀማኛን ቢከላከልም ቀማኛ ከመባል አይድንም:: ደግነቱ ለህዝብ እንጅ ለቀማኛ የቆሙ ፖለቲከኞች እንደሆኑ አስቀድሞም ህዝቡ ያውቃልና የሚፈጠር ነገር የለም፡፡
በራሳቸው በመስራች አባላቶቻቸው የአሰራር ወይም መረጃ ክፍተት የተነሳ የሚወዛገቡ አካላት እንኳን ጥቅሞቻቸውን የማያጡበት እና መንግስትም ሂደቱን የሚቆጣጠርበት ህግና ስርዓት ስላለው ህግን የተከተለ ነገር ሁሉ ማንንም ስጋት ውስጥ እንደማይከት መረዳት ይቻላል፡፡
ከዚህ አንጻር ያነሳነው አክሲዬን ማህበርም ቢሆን አሰራሩን ተከትሎ የተበላሸም ካለ በማረም፣ ያጠፋም ካለ በመቅጣት የብዙሃኑን ዲያስፖራ ጥቅም ለማስከበር መንግስት እንደሚሰራ እምነታችን ነው፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ አባላቱ ያዋጣችሁት ገንዘብ አሁንም በአስተማማኝ እጅ ላይ እንዳለ በማመን ትክክል አይደለም የሚባለውን ሂደት ሁሉ በማስተካከል ያለማችሁለትን ግብ ማሳካት አለባችሁ፡፡
በነገራችን ላይ ቀደም ብዬም እንዳልኩት ከእንደዚህ አይነቱ ሂደት በመማር ጥንቃቄ በማድረግ ወደ ልማት ስራ ለመግባት የሚያስችሉ እና የዲያስፖራውን የመረጃ ክፍተት የሚሞሉ መድረኮች እየተፈጠሩ ነው፡፡በተለይም በዋሽንግተን የኢትዬጵያ ኤምባሲ ዲያስፖራው በግሉም፣ በጋራም ከውጭ ኢንቨስተሮችም ጋር በመሆን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ ከመቸውም ጊዜ በላይ ወገቡን አስሮ እየሰራ ይገኛል፡፡
ቀደም ባሉት ፕሮግራሞቻችን እንደገለጽንላችሁ በተለይም አምባሳደሩ በተለያዬ ስቴቶች በመንቀሳቀስ ዲያስፖራውን የማወያየት ተግባር ሲያከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ ጉዳዬ የሚመለከታቸውን ዲፕሎማቶቻቸውን መድረኮችን እንዲፈጥሩ በማድረግ በርካቶችን በሃገራቸው ልማት ላይ ለመሳተፍ ሰርተዋል፡፡
ከምንም ነገር በላይ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት የመንግስትና ሃገርን ፍላጎት እና ተጨባጭ እውነታዎች ተቀራርቦ በመወያየት የሚመጣው ለውጥ ከፍተኛ ነው፡፡ መወያየት ሲጀመር መተማመን፣ መተማመኑ ደግሞ መደጋገፍ እና ለውጥ ማምጣትን እንደሚፈጥር እሙን ነው፡፡
በቅርቡም ራሳቸው አምባሳደር ግርማ ብሩ ወደ ሂዬስተን ቴክሳስ በማምራት በዚያ ከሚኖሩ በርካታ ኢትዬጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዬጵያዊያን ጋር በሃገራቸው ጉዳይ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡ በዚያ መድረክ በወቅታዊ የሃገራችን ጉዳይ ላይ ግልጽነት ከመፍጠር ባሻገር ዲያስፖራው ወደ ኢንቨስትመንት የሚያስገባውን ምቹ ሁኔታ እና ጥቅሞቹን በተመከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ውጤታማ ስራ ሰርተዋል፡፡
ዛሬ ላይ ወደ ሃገራችን ሄደው ኢንቨስትመንት ውስጥ የሚሰማሩት ኢትዬጵያዊያን ቁጥር የሃገራችን ሰላም እና እድገት ስበቱ ጠርቷቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ኤምባሲው እንዲህ አቅዶ ሲሰራበት ቁጥሩ በዚያው መጠን እንደሚጨምር እያየነው ነው፡፡
እናም ኤምባሲው ለሃገራችን ከውጭው አለም ጋር ለመገናኜት ያለን ድልድይ ብቻም ሳይሆን በውጭ ለምንኖረውም የለውጥ በር ነውና የግልጽነት ጥያቄዎቻችን ከመመለስ ጀምሮ ሂደቱን እስከማስተባበር ድረስ ያለውን ተግባር በመጠቀም እንሳተፍ፣ እናልማ፣ እንለወጥ፣ እንለውጥ፣ መልእክታችን ነው፡፡

03161071
Today
Yesterday
This Month
Last Month
All days
2991
4118
86584
75600
3161071

Since April 1, 2014

Photo Gallery