You are here: HomeARTICLESእኛ የመጀመሪያዎቹ በሰለሞን ተካልኝ፣ የሃገር ቤት ወግ

እኛ የመጀመሪያዎቹ በሰለሞን ተካልኝ፣ የሃገር ቤት ወግ

Published in Articles
Rate this item
(1 Vote)

እንደው ከሰሞኑ የሃገር ቤት ጉዳይ ከአዲስ አበባ ፒያሳ ግድም አንድ ሃይገር የተባለ የከተማ ባስ ልጓሙ እምቢ ብሎት ቁልቁል እየተንደረደረ ያገኜውን ሁሉ እየደረማመሰ መጨረሻ ላይ ሲወድቅ ሁለት ሰዎችን መግደሉን ስሰማ አንጀቴ በሃዘን ብጥስ ነው ያለው፡፡
መቼስ የመኪና አደጋ ለአዲስ አበባም ሆነ ለሃገራችን ህይወት ሲበላ እደሚከርም እየሰማን ብንኖርም ይህ አደጋ በደረሰ ማግስት ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የአውቶቡስ መንደርደሪያ ዘመናዊ መንገድ ሊሰራ ነው ሲባል ሰምቼ ኸረ እባካችሁ ቶሎ ቶሎ እንዲህ ዘመናዊ መንገዶችንም ዘመናዊ መኪኖችንም እያስገባችሁ አዲስ አበቤን ሁሉ እፎይ አስብሉት ብያለሁ፡፡
መቼም እኔ ወሬ መደበቅ አልችልም፡፡ የሰማሁትን ልንገራችሁ፡፡ ከዊንጌት እንከ ጀሞ 16 ኪሎሜትር የሚረዝመው ይኸ የአውቶቡስ ብቻ የሆነ መንገድ በሁለት ቢሊዬን ብር በ26 ወራት ተገንበቶ የሚያልቅ ነው አሉ፡፡ ተፈረንይ መንግስት ጋር ሃገራችን በገባችው ውል መሰረት ሸገር ወደፊት 7 ተመሳሳይ የአውቶቡስ ፈጣን መንገድ ሲኖራት በአፍሪካ የመጀመሪያም ትሆናለች ተብሏል፡፡
የመጀመሪያ ስንል እንግዲህ የሚቆረቁራችሁ ሰዎች ቻሉት፡፡
ማራቶንን በባዶ እግር በመሮጥ በአለም የመጀመሪያ የመሆናችንን ያህል የአውቶቡስ ዘመናዊ መሮጫ በመስራትም በአፍሪካ የመጀመሪያ መሆናችን ነው እንግዲህ፡፡
አሮጌ አውቶቡሶችን በከተማችን የማዘዋወራችንን ያህል በኮምፒዬተር የታገዙ በራሳቸው መም ላይ የሚሮጡ ዘመናዊ አውቶቡሶችን በማስመጣትም የመጀመሪያ ልንሆን ነው ማለት ነው፡፡
በሉ እንግዲህ እኔም እዚህ ላይ የመጀመሪያ የወግ እርሴን በዚሁ ልቋጭና ወደ ቀጣዬ የወግ እርሴ ልሂድ፡፡
መቼስ ዛሬ የመጀመሪያ የሚለውን ሃሳብ ታጥቄው ነው የተነሳሁት፡፡
ከሰሞኑ የጣሊያኑ ፕሬዘዳንት ወደ ሃገራችን ለአምስት ቀናት የስራ ጉብኝት መጥተው መመለሳቸውን ስሰማ የአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ትዝ ብሎኝ የቁጥሮቹ መገጣጠም ለምን ይሆን እያልኩ ነበር፡፡
ለማንኛውም አድማጮቼ እንደው የፕሬዘዳንት ሰርጅዬ ማቴሬላን የስራ ጉብኝት በሃሳቤ እያኜክሁ ነጮችን በጦርነት ሜዳ ላይ የረታን የመጀመሪያ ጥቁር ህዝቦች እኛ መሆናችንን ማሰቤም አልቀረም፡፡
ታዲያ በዚያ የመጀመሪያ የጥቁር ህዝቦች ድላችን ያፈረው ጣሊያን ድጋሜ ሲመጣ እስክናባርረው አምስት ዓመት ፈጅቶብናል፡፡ በዚያ አምስት አመትም ጣሊያን ብዙ እንደፈጀን በፕሬዘዳንቱ የአምስት ቀናት ጉብኝት ጊዜ በዜና ስሰማ እርግጥ ነው የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት የካቲት 12 በዋለ በያመቱ ነፍስ ታወቅሁ አንስቶ ስሰማው ኖሬያለሁ፡፡
በዚያ አምስት ዓመት የጣሊያን የብቀላ ወረራ ጊዜ በተለይም ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ተወረወረ ተብሎ እልፍ አበሻ ህይወቱን ተነጥቋል፡፡ በቀናት ውስጥ ብቻ ሽዎች ከህይወት ወደ ሞት ተሸኝተዋል፡፡ ይህ አሳዛኙ የሃገራችን እጣ ፋንታ ነው፡፡
እንዲያ ያለው ግፍ በጣሊያን ሲፈጸምብን አለም በቸልታ ቢመለከተንም አርበኞች ግን ጣሊያንን መውጫ መግቢያ እስኪያጣ በዱር በገደል እየተከታተሉ ተግትገውታል፡፡
ያም ሆኖ እንደው በወጋችን መካከል የትላንቱን ግፍ እዚሁ ላይ ገትተን የዛሬውን የኛና ያጣሊያንን ጉዳይ ስናነሳ ከዘመኑ ጋር ያለፈውን እረስተን የትላንቱን ለታሪክ ትተን ነገን በዛሬ ውስጥ ለመኖር አብረን እየሰራን ነው፡፡
እንዲህም ሆኖ ስድስት ኪሎ የተገኙት ፕሬዘዳንቱ በየካቲቶቹ ሰማእታት ሃውልት ስር ትልቅ የአበባ ጉንጉን ሲያስቀምጡ በጣሊያን መሪ ደረጃ  በትልቅነታቸው የመጀመሪያው ሳይሆኑ እንደማይቀሩ እገምታለሁ፡፡
ግን እንደው ክቡር ፕሬዘዳንቱ ትልቁን አበባ በዚያ ሃውልት ስር ሲያስቀምጡ በነጭ ጠጉራቸው በተሸፈነው አእምሯቸው ውስጥ የመጣው ሃሳብ ምን ይሆን?
ግራዚያኒን አፈር ብላ ብለውት ይሆን ወይስ ምስኪን ወገኖቻችንን አፈሩ ይቅለላችሁ  ብለው ይሆን? ለማንኛውም መጥፎ ታሪክን በጥሩ ስራ እንጅ በሞጥፎ ትውስታው ትርፍ የለውምና ፕሬዘዳንቱን ስላከበሩን ደስ ብሎኛል፡፡
መቼስ ዛሬ በሃገር ጉዳይ የኛና የጣሊያን ጉዳይ ከትላንቱ ጋር የማይገናኝ የተራራቀ ማለቴ ቦሌና ጉለሌ መሆኑን እያየነው ነው፡፡
ጣና በለስን፣ ጊቤን አባይን የሚገድበው ሳሊኒስ እንዲህ ወገቡን አስሮ እየሰራ ትብብራችንን በብቃት እየገደበው አይመስላችሁም፡፡
እኔ መቼስ በዚህ ደስተኛ ብንሆን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ መጥፎ ስራዎች ከሰሪዎቻቸው ጋር ከተቀበሩ ሬስት ኢን ፒስ ብለን ነው ማለፍ ያለብን፡፡
አሁን አንዳንዶቻችሁ፣ ፕሬዘዳንቱ አበባ ሲያስቀምጡ “አበባህ ይርገፍ! ትላንት የሰራኸውን እረስተህ ነው ዛሬ እንዲህ የምትሆነው” እንዳላችሁ ሰምቻለሁ፡፡ በጣሊያናዊነቱ ብቻ ፕሬዘዳንት ሰርጅዬ ማቴሬላ ሞሶሎኒን ሊወክል እንደማይችል ማወቅ ያለብን አይመስላችሁም፡፡ እውነቴን ነው፡፡ ሰው በደሙ ወይ በሃገሩ ብቻ ሚዛን ላይ ተቀምጦ ሊመዘን አይገባውም፡፡ በአስተሳሰቡ እንጅ….
እናም ሰውን እና ሃሳብን ለያይተን ካላየን ጀርመናዊያንን በሂትለር፣ ጣሊያናዊያንን በሞሶሎኒ፣ አይን ማየቱ እይታችንን በራስ እጅ እንደማንሸዋረር የሚቆጠር ነው፡፡
መቼስ ፕሬዘዳንት ሰርጅዬ ማቴሬላ ኢትዬጵያን ዞረው የቱሪስት መስህቦቻችንን ጎብኝተው ከመሪዎቻችን ጋር ተወያይተው ሲመለሱ እንደሃገር ብዙ እንደምናተርፍ ግልጥ ነው፡፡ ግን እንደው እናንተዬ ይህችን ውድ ሃገራችንን ካላየናት ብለው አየሩን ባውሮፕላናቸው እየሰነጠቁ የሚመጡት አውሮፓውያን፣ አሜሪካዊያን እና ሌሎችም መሪዎች መብዛታቸው እንደ አንድ ሃገርኛ ሰው ኩራቴን አብዝቶታል፡፡
እንግዲህ ሌላኛው ግዘፍ አውሮፓዊ መሪ የእንግሊዙ ዴቪድ ካሜሩንስ መምጫቸው ደረሰም አይደል?
ኸረ እናንተዬ ከዚህም ከዚያም ወደኛ የሚሄደው በዛ! እንደው እናንተስ ሃገርኛየምትሉት፣ ነን መቼ ነው የምትሄዱት?
እውነቴን እኮ ነው የማያውቁን ሌሎች ፈልገውን ሲሄዱ የኛዎቹ ግን የራሳችሁን ጉዳይ ራሳችሁ ከማንነታችሁ እንደራቃችሁት እስከመቼ ትኖራላችሁ? በዚህ ጉዳይ ላይ በዚህ የሃገር ቤት ወጋችን ሳናወጋ ማለፍ ነውር ሆኖብኝ ነው እኔ ይህንን የምለው እንጅ ከሃገር ብቻ ሳይሆን ከራሳችሁም የተጣላችሁት አንዳንዶቻችሁ እንኳን ለይቶላችኋል፡፡
ራሳችሁ ጠፍቶባችሁ የምትፈልጉት ሌላውን ነው፡፡ እኔ ምለው ግን ራሳችሁ ከራሳችሁ ከተጠፋፋ የትኛው ማንነታችሁ ነው ፍለጋ ላይ ያለው? ማለቴ ከራሱ የጠፋ ሰው እንዴት ነው የሚያወራው ወሬ፣ የሚያምነው እምነት፣ የሚናገረው እውነት፣ የሚኖረው ህይወት የራሱ የሚሆነው፡፡
እንደው ጉዳዬን የበለጠ ግልጽ ላድርገው እና ስለሃገር እና ህዝብ ለመተቼት እና ለመቆርቀር የሚሞክሩ ግን ደግሞ ለሃገር ሳይሆን ለሃገር ጠላት የተገዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በግልጥ አማርኛ ምን ማለት ነው፣ ለሁለት ጌቶች የተሸጠ ባሪያ ማለት ናቸው፡፡ ባንድ በኩል የሃገር ፍቅር እንደሳት የሚያነደን ነን ይላሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚሁ ሰዎች በገንዘብ ፍቅር ልባቸው የነደደ ነው፡፡
ገንዘቡ የሚገኜው ደግሞ ሃገርን በማዋረድ እና ጡት በመንከስ ነው፡፡ የእናትህን ጡት ንከስልኝና አሳምማትና ከቻልክም የጡጧን ጫፍ ቁረጥ እና ገንዘብ ታገኛለህ የተባለ ነካሽ፣ አፉ የናቱን ጡት እስኪይዝ ድረስ የሚጮኸው ስለእናቱ ፍቅር እንደማለት ነው፡፡
የእናቱን ፍቅር እንደ አዋጅ የሚጮኸው ጥርሶቹ ጡቶቿን እስኪነክስ ነው፡፡
ጅብ አስኪነክስ ያነክስ እንደሚባለው” ማለት ነው እንግዲህ፡፡ በነገራችን ላይ ባብዛኛው “ሃገሬ….እምዬ…ጡተ ረዥሟ…እናቴ....ማርና ወተቴ….እንትና እነእንትና ገደሉሽ በደሉሽ…..” በሚል ሲንጫጩ የምንማቸው እኒሁ ጡት ለመንከስ የተከፈላቸው ናቸው፡፡
ሌላው አብዛኛው ሃገርኛ አንድም በዝምታ፣ ሁለትም በግርምታ ጤንተታቸውን እየተጠራጠረ እነዚሁን የሚመለከት ነው፡፡
እኔ ራሴ ስንትና ስንት ቀን ወይ ለጠበል ሸንኮራ፣ ወይ ለህክምና አማኑኤል አግኝቼ በወሰድኳቸው ብዬ ተመኝቻለሁ፡፡
መቼስ ይኸ የሃገር ቤት ጉዳይ አይደል፡፡ እንዲህ አይነቶችን ካገኛችሁ ህመማቸው እንዲለይላቸው ስለሃገርራችሁ እድገት፣ ስለህዝባችሁ ለውጥ እና የቀደመውን ታላቅነታችንን እየመለስን እንደሆነ ንገሯቸው፡፡ ያኔ ጠበል እንደነካው በሽተኛ ሲለፈልፉ ታዬአቸዋላችሁ፡፡
በነገራችን ላይ የዚያ የጡት አስነካሹን ሽማግሌ ጉዳይስ ሰምታችኋል፡፡ እንዴ! በጣም ብዙ ወታደሮቹ ከነ ትጥቃቸው ሎጋው ሽቦን እየጨፈሩ ሱዳን ገቡ አሉ፡፡
አይ እንደው እኝህ ሰውዬ “ከሞቴ አሟሟቴን አሳምረው” ብለው አልጸለዬም ልበል፡፡ ነው ወይስ በአረብኛ እንዲህ አይነት ጸሎት የለም? እንደው እኔማ የኤርትራዊያን ዜጎች ሳያንስ እንዲህ ወታደሩ በጋንታ እና በሃይል እየተናደ ሲሄድ ይኸ ሽማግሌ ምን ይውጠው ይሆን እያልኩ ነበር፡፡ እንደው ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋልና፣ ይህንን በመቶ የሚቆጠሩ የሻእቢያ ወታደሮች ወደ ሱዳን መክዳት የሰማ አንድ ወዳጄ ምን አለ መሰላችሁ፣ “ራሱ ኢሳያስም እኮ ቢችል ይከዳ ነበር፣ ችግሩ ከማን እንደሚከዳ ግራ ገብቶት ነው” ሲል ጨዋታ ቀጠለ፡፡
እርግጥ እርሱ ከማን እንደሚከዳ ግራ ቢገባውም አሁን የተጀመረው ክዳት ግን መሬት እንደከዳው ያህል የሚከብድ መሆኑ አይቀርም፡፡
እንደው በሽማግሌ ትከሻ እንዲህ ያለውን ነገር እንዴት ቻሉት ወዳጆቼ?!
የሆነስ ሆነና እናንተዬ፤ ይኸ አሁን ያለንበት ወር ወርሃ መጋቢት መሆኑን አስባችሁት ይሆን? ይኸ ወር መቼም ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት ለኢትዬጵያዊያን ለለውጥ የምስራች ስንሰማ በጣም አስገራሚ እና አስደናቂ ነገሮችን የሰማንበት የመጀመሪያው ወር ሳይሆን አይቀርም፡፡
ማለቴ የመጀመሪያ ስል በዘመነ ኢህአዴግ ከተከናወኑት የልማት ስራዎች ሁሉ በግዝፈቱ እና በትኩረት ማግኜቱ የመጀመሪያ የሆነውን ስራ መጀመሩን የሰማንበት ነው ብዬ ነው፡፡
ይኸ አባይን የመገደብ የዘመናት ፍላጎታችን በይፋ መጀመሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው በወርሃ መጋቢት 24ኛው ቀን ላይ ነው፡፡
እንደምታስታውሱት የልብ ትርታችንን የጨመረውን ዜና ከጉባ በረሃ ከአምስት አመት በፊት አባይ እንደሚገደብ የሰማነው በወርሃ መጋቢት ነበር፡፡
ታዲያ ይኸ የመጀመሪያ ብለን ከምንጠራው ስራችን ውስጥ አንዱ ለመሆን የበቃው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ የመጀመሪያው በዓለም ስምንተኛው ግዙፍ ግድብ መሆኑ አይቀርም ተብሏል፡፡
በዚህ ዓመት ግድቡ ቁመቱ አድጎ 75 ሜትር ገደማ መድረሱንም ሰምተናል፡፡
እንርግጥ ነው አድማጮቼ እንዲህ ያለውን ሃገርኛ ጉዳይ ጊዜው ሲደርስ በሰፊው የምንመክርበት ሆኖ ለዛሬ ግን እንደው የመጀመሪያ በሚለው ማእቀፍ ውስጥ ሳላነሳው እንዳላልፍ ብዬ ነው፡፡
ለማንኛውም እናንት የሃገር ቤት ወግ ታዳሚዎቼ እኛ የመጀመሪያዎቹ ኢትዬጵያዊያን “የመጀመሪያ” የሚለውን ቃል ስለምንወደው ብቻም አይደለም በነገራችን ሁሉ የምናስቀድመው፡፡
በእርግጥም በብዙ ነገር የመጀመሪያዎች በመሆናችን ነው፡፡
ሰው ዘሩ ተገኘ ተብሎ አጥንት ተመርምሮ እድሜ ሲቆጠር በእርጅና የመጀመሪያ እምንሆን፡፡ ሃገር አደገ ተብሎ ቆመን ከነበረበት ሩጫችን ካሯሯጣችን ሲመዘን በፍጥነት የመጀመሪያ የምንሆን፡፡
ታሪካዊ ጀግኖች ተብለን የጣልነው ግዳይ ተመዝኖ ከፈሪዎች ጋር ስንወዳደር ጀግንነታችን የመጀመሪያ የሚያስብለን፡፡
ብቻ በብዙ ነገራችን የመጀመሪያ ለማለት በታሪካችንም በማንነታችንም በመንገዳችን ሁሉ የማይቸግረን ለኩራታችን መነሻ የማናጣ ዜጎች ነን፡፡
ደግሞ የአለም ጅኦግራፊያዊ አከላል ለዚህ ጠቅሞናል፡፡
ከአለም የመጀመርሪያ ስንሆን ችግር የለውም፡፡ ባንዳንድ ጉዳዬች ግን ከአለም የመጀመሪያ መሆን ባንችል ከአፍሪካ የመጀመሪያ እንሆናለን፡፡
ይህም ጥሩና ምርጥ የሚባል መሳፈሪያ እና መለካኪያ መንገድ ሆኖናል፡፡
በሰላም ማስከበር ከአለም ሶስተኛ ከአፍሪካ መጀመሪያ ነን፡፡
መቼስ ይኸ የሃገር ቤት ወግ አይደል ጉዳዬ በወግ ለዛ ተዋዛ እንጅ ደረቅ እውነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እንደው ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ የመጀመሪያ መሆንም አይቻልም እንዲያ ቢሆን ኖሮማ ራሱ የመጀመሪያ የሚለው ቃልም ባልነበረ ነበር፡፡
ግን ደግሞ የቀደሙትም ያሉትም በሰሩት ደጋግ ነገር ሁሉ”የመጀመሪያን” ከትላንት እስከዛሬ በታሪካችን ውስጥ እያንከባለልናት ይኸው ዛሬን ደርሰናል፡፡
እንደው በጨዋታችን ላይ ግን በጥሩ ነገር ወይም በስኬት መለኪያ የመጀመሪያ የሆንባቸውን ነገሮች ያህል በተቃራኒውም የመጀመሪያ የሆንባቸው ጉዳዬች አይጠፉም፡፡
መቼስ ይኸ ጥቁር አፈር የአፍሪካ ምድር ስንት ጥቁር ታሪክ አለው መሰላችሁ፡፡
እኛም ከዚሁ ከጥቁር አፈር ላይ ከበቀለው አመዳም ታሪክ መውጣት አንችልም፡፡ ለምሳሌ ካለፈው ታሪካችን ብንነሳ የእርስ በእርስ ጦርነት እና እርሃብ በስፋት ያስተናገደች ሃገር ተብሎ ደረጃ ቢወጣ አሁንም የመጀመሪያ የሚለውን ደረጃ መያዛችን አይቀርም፡፡
ለማንኛምውም ግን አሁንም በዚሁ በጥፋቱ ጎራም “የመጀመሪያ” ሊያደርጉን የተሰለፉ “ተከፋይ ጡት ነካሾች” አሉና እነሱን ከመካከላችን በማውጣት እኛ የመጀመሪያዎች እንሁን፡፡
ታሪካችን፣ እና ማንነታችን ለነገው ቀዳሚነታችን ወሳኝ መስፈንጠሪያ ነውና እኛ የመጀመሪያዎቹ ከስኬት እንዳንቆም ሃገርኛ ሃሳቤን ተቀበሉኝ፡፡

03161065
Today
Yesterday
This Month
Last Month
All days
2985
4118
86578
75600
3161065

Since April 1, 2014

Photo Gallery