You are here: HomeARTICLESአስመራ የቀረው የግንቦት 7 አመራር አንድ ብቻ ነው፡፡ በሰለሞን ተካልኝ ከጽናት ራዲዬ

አስመራ የቀረው የግንቦት 7 አመራር አንድ ብቻ ነው፡፡ በሰለሞን ተካልኝ ከጽናት ራዲዬ

Published in Articles
Rate this item
(2 votes)

ከወራት በፊት ባለፈው ዓመት የግንቦተኞቹ ሊቀመንበር “ትግሉ ነው ህይወቴ” ብሎ አስመራ ሲዘምት እነ ኢሳት ብቻ ሳይሆኑ ታላላቅ ነን የሚሉት ሚዲያዎችም ነገሩን እራግበውት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
እኛም በመልእክተ ሰለሞን ዝግጅታችን በውዳሴ ከተራገበው ሃተታ በተቃራኒው “ዱርየው ዱር ገባ” በሚል እርስ በዚህ ወቅት እንደሚመለስ ጭምር ዘግበን ነበር፡፡
`ይሄ ሰውዬ በጃንዋሪ 2016 ክላስ አለብኝ ብሎ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነን` ማለታችን ይታወሳል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከኢሳት እስከ ቪኦኤ ራቁታቸውን ያስቀረውን መረጃ ከሰሞኑ ከዶክተር ብርሃኑ ዬንቨርስቲ ፈልፍለህ ያወጣኸው ጋዜጠኛ መስፍን በዙ ምስጋና ይግባህና ዶክተር ብርሽ አስመራ የዘመተው የሃሰት የህክምና ፈቃድ ከሚያስተምርበት ቡክኔል ዬንቨርስቲ ለስድስት ወር ሞልቶ መሆኑን አስረግጦ አረጋገጠልን፡፡
በጣም ይገርማል አልልም መቼም፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ዱርዬ የሚጠበቅ የማጭበርበር ወንጀል ስለሆነ ብዙ የሚገርም አይደለም፡፡
ይህንን መረጃ የሚጠራጠር ካለ ወደ ዬንቨርስቲው ድረ ገጽ ገባ ብሎ (ከቡክኔል ዬንቨርስ) በ2015/2016 ፈቃድ ወስደው የወጡትን አስተማሪዎች ዝርዝር ማግኜት ይችላል፡፡ በመረጃው መሰረት ምንደኛው አርበኛ ዶክተር ብርሽ አስመራ የዘመተው ከነ ደምወዙ ነበር ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ የዬንቨርስቲው ቃል አቀባይም ዶክተርዬ ስራ እንዳልለቀቁም አረጋግጧል፡፡ “የነጻነት ተሟጋቹ፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው አርበኛው እና ህይወቱን ለትግል የሰጠው” ሰው ታሪክ እንዲህ ነው እንግዲህ፡፡ በማጭበርበር እና በቀልድ የተሞላ፣ በሌሎች መስዋእትነት ትርፍ የሚያጋብስ ቀላል ቀልደኛ እና ፎጋሪ አታላይ ነው፡፡
ባንድ ወቅት የቀድሞ (በቅንጅት ዘመን) የትግል አጋሩ የነበረውን አቶ ልደቱ አያሌውን ኢንተርቪው በጽናት አድርገነው “እግዚአብሔር ኢትዬጵያን ይወዳል፣ እንደ ብርሃኑ አይነት ሰው ስልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮ በሃገራችን ከደርግም ዘመን የከፋ እልቂት ያመጣ ነበር፡፡ ሰውየው ከኢህአፓ ግዜ ከድቶ በድርጅቱ የታሰረ….አጭበርባሪ ጭምር ነው” ማለታቸውም ይታወሳል፡፡
እናም ቀድሞም ዘንድሮም በዚህ የማጭበርበር ተግባሩ የገፋበት “ሊቀመንበር” ከሰሞኑም ዋሽንግተን ላይ ሳቅና ቀልድ አብዝቶ ከዚህ በፊት የማይታይበትን ዋዘኛነት በንግግሩ ሲያንጸባርቅ ተስተውሏል፡፡
ማለቴ የሳቸው ዋዘኛነት እና ፉገራ በተግባራቸው ነበር እንጅ ንግግራቸው ሁልጊዜም በፉከራ እና በቁጭት ነበር፡፡ በዚያ ያዛውንቶች ክበብ ውስጥ ባደረጉት ንግግር ግን የማይታወቁበትን ቀልደኛነት እያሳዬ ላያቸው “ሰውየው ኮሚክነቱን ከታማኝ ነጠቁት እንዴ?” ያሰኝ ነበር፡፡
እኔ ራሴ ታማኝና ብርሽ ቦታ የተቀያየሩ ነበር የመሰለኝ፡፡
ለካስ ዶክተርዬ እንዲያ መላጣቸውን እያሳከከ በፌዝ የሚያስወራቸው መሄድ መምጣታቸው ውስጥ ያለው የራሳቸው ፉገራ ነበር፡፡
አንዳንዴ እኮ እንዲህ ነው፡፡ እየሞቱ ማልቀስ…እየሳቁ ማልቀስ ይገጥማል፡፡
መላጣ የሚያሳክክ፣ በትግል ወግ ውስጥ የሚያስቅ፣ በቁምነገር መሃል ፌዝ ሚያስመርጥ እሱ የመጨረሻው ዘመን ነው ለካ!?
ዶክተር ብርሽ ደምወዝተኛው አርበኛ ሳቅ ሳቅ ያላቸው ለካ ያለ ምክንያትም አልነበረም፡፡ “ትግሉን ይተዋል ብላችሁ የምታስቡ ራሳችሁን አታለላችሁ” ሲሉን መላጣቸውን እያከኩ እና እየሳቁ ነበር፡፡ ለካ የሚያስቅ የሚያሳክካቸው ዬንቨርስቲው የሰጣቸው የፈቃዳቸው ቀን ማለቁን አስታውሰው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ደግሞ ኮ “ትግሉ ሰሜን ውስጥ(ኤርትራ) ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም ቦታ አለን፣ አሁን ትግላእን እዚህ ነው” ሲሉ ስሰማቸው “እዚህ” የምትለው ቃል (ዋሽንግተን) ከዚህ አልመለስም ለማለትም ጭምር እንደሆነ የገባን ቆይቶ ነው፡፡ የመስፍን በዙን ማጋለጥ ስንሰማ፡፡ አልመለስም አታስቡት እያስተማርኩ እቀልዳለሁ ለማለት ፈልገው ነው፡፡
ይኸው አሁን ጊዜው ደርሷል፡፡ ዋሽንግተንም ውስጥ እያስተማሩ መታገል ይቻላል እንደሚሉ ከወዲሁ ተረጋገጠ ማለት ነው፡፡
ውሸት ከአውሮፓ ህብረት እስከ ዋሽንግተን ዬንቨርስቲ በጽንፈኛው ወሬ አቀናባሪዎች እና በፓርላማ አባሏ ሃና ጎበዜ እገዛ እንደቀጠለ ቢሆንም ገመናው እየተጋለጠ ራቁትነታቸው እየፈጠጠ መጥቷል፡፡
እንዲህ ሆነ የሊቀመንበሩ መጨረሻ የቅሌት ደረጃ፡፡ አሁን እሳቸው ካልተመለሱ አስመራ የቀረው የቡድኑ አመራር አንድ ብቻ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ለመሆኑ እሱ ማነው አስመራ የቀረው? የሚለውን ከማየታችን በፊት አንድ ስንኝ ላስታውሳችሁ እና ቅድመ እና ድህረ ዘመቻውን እንመልከተው፡፡
“ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
ሃገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ” እንዲል ዘፋኝ፤
ከሃገሩ የወጣ ሃገሩ እስቲመለስ፣ ሃገሩን የናፈቀ ቀየው እስቲገባ ያያዘውን ናፍቆት የሚያስወጣ ምርጥ ዘመን አይሽሬ ዘፈን ነው፡፡
በተለይ ትውልደ ኢትዬጵያዊው እና ኢትዬጵያዊው ብቻ ሳይሆን ሃገሩን ለማየት የጓጓ ሁላ እንዲህ ያለው ዜማ ስሜት ኮርኳሪ እና ሆድን የሚያሸብርም ጭምር ነው፡፡
ግን ደግሞ አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ያለውን ትልቁን ወንበር በመሻት ብዙ ርቀው የቆዬ ስልጣን ፈላጊዎች ደግሞ ናፍቆቱ ምን ያህል ጠንካራ ሊሆንባቸው እንደሚችል እናንተው ገምቱት፡፡
የአዲስ አበባዋ አራት ኪሎ ጊቢ ውስጥ ያለውን ወንበር ሽተው መጀመሪያ በሸፍጥ በኋላ በነፍጥ የሞከሩት ግንቦት ሰባቶች አዲስ አበባ ቅርብም ሩቅም ሆና ቆይታባቸዋለች፡፡
ለዘመቻ ወደ ኤርትራ ሲወጡ አዲስ አበባ ከዋሽንግተን የሩቅ ቅርብ ነበረች፣ ያኔ መንገዱም ቁልቁለት ነበር፡፡
እንደው ለአፍታ ተንደርድረው አራት ኪሎ እንደሚገቡ ያለሙት እነ ዶክተር ብርሃኑ “መጣን ጠብቁን፣ እናንተ ጋር እስክንደርስ ሳምንት ብቻ….” ብለው ፊሽካ መንፋታቸውን ታስታውሳላችሁ፡፡
ያኔ ለግንቦት ሰባቶች መንገዱ ቁልቁለት ነበር፡፡ ሻእቢያዎችም በቁልቁለቱ ላይ ምንም እንቅፋት እንደማይገጥማቸው ምሎላቸው ነበር፡፡ አረቦችም ቢሆኑ “አይዟችሁ አለን” ሳይሉ አይቀሩም፡፡ እናም የፈሪ ፎካሪ የሚፎክረው ሳይገል ነውና ገና በፊሽካ ህዝቡን ጠብቁን ብለው ብዙ ደጋፊዎቻቸውን እና ሎሌዎቻቸውን ሻንጣ አስጠቅልለዋቸው ነበር፡፡
አዲስ አበባ ከዋሽንግተን በቁቁለት ጉዞ ቀርባ፣ ሩቁዋ አዲስ የሩቅ ቅርብ ሆና ታይታቸው መንደርደራቸው የቅርብ ትዝታ ነው፡፡
ዛሬ ግን ሁሉ ነገር አልፎ ከዘመቻ ሲመለሱ አዲስ አበባ የቅርብ ሩቅ፤ ህልማቸው ብቻ ሆና ቀርታለች፡፡
መቼም ያኔ “ቁልቁለት ልንደረደር ነው” ያሉት እነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ትላንት ያሉትን ዛሬ ሲያስቡ ምን እንደሚሰማቸው መገመት ባልችልም ቁልቁለቱ ድንገት ዳገት ሲሆንባቸው ግን ድንጋጤያቸው ልክ እንደሚያጣ አልጠራጠርም፡፡
ሲሄዱ ቁልቁለት ሲመለሱ ዳገት የሆነው የከሸፈው ዘመቻ ጉዞ በኢሳት የማስተባበያ ዜና ብቻ ሰባራው የሚጠገን አይነት ግን አልሆነም፡፡
ግንቦት 7ቶች ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆመው ማውረድ ቸግሯቸው ዛሬም በድብርት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ሻእቢያም ቢሆን በጣም አስገራሚውን ታሪካዊ ክህደት ፈጽሞባቸዋል፡፡
ለነገሩማ በራሱ ህዝብ (በኤርትራዊያን) ላይ ክህደት ለመፈጸም ችግር የሌለበት ሻእቢያ እንዴት ግንቦተኛ አርበኞችን አይከዳቸው፡፡
እነሱ ወደ አዲስ አበባ በቁልቁለት እየተንደረደርን ነው ብለው ባለሙ ቅጽበት መንደንደራቸውን ሳይጀምሩ ገና፣ አስማት በሚመስል መልኩ ቁልቁለቱን ዳገት አድርጎባቸው ቁጭ አለ፡፡
“ያሳዝናል”፡፡ እርግጥ ነው ጉዳዬን ከአላማና አቋም አኳያ በግልጽ ከስሩ ላጤነው በሻእቢያም የሚፈረድ አይመስለኝም፡፡ ሻእቢያ የሚመራትን ሃገር ነጻነት ሉዋላዊነት ድጨ ከኢትዬጵያ ጋር እጨፈልቃለሁ የሚልን አፈኛ የግንቦት ሰባት ቡድን በጭቃ ቢገርፈው የሚገርም አይደለም፡፡
ይልቅ የሚገርመው ዳገትና ቁልቁለት መለየት ያልቻሉት “የምሁራን ታጋዬች” እይታ ነው፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ፣ ዳገትና ቁልቁለት የማይለዬ ፊሽካ ነፊዎች ናቸው እንግዲህ ሃገር ሊመሩ ነፍጥ አንስተናል ብለው ሲፎክሩ የከረሙት፡፡ ለነገሩማ እንኳን ዳገትና ቁልቁለት ይቅርና ፊሽካና ድሽቃ እንኳን መች ይለያሉ ብላችሁ ነው፡፡ (ድሽቃ ምንድን ነው ለምትሉ አድማጮች ድሽቃ በትከሻ ተወድሮ የሚተኮስ ትልቅ ተወንጫፊ ያለው መሳሪያ ነው እላችኋለሁ፡፡)
ዶክተር ብርሃኑ አስመራ ከመዝመታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው ጦርነቱን ሲጀምሩ ያሉትን መቼም ታስታውሱታላችሁ፡፡
ድሽቃ ትከሻቸው ላይ አድርገው ጥይት የተኩሱ መስሏቸው “የጦርነቱ ፊሽካ ተነፍቷል” አሉ፡፡ አየ “አ - ርበኞቹ”! “የጦርነቱ ድሽቃ ተተኩሷል” ለማለት ፈልገው ነበር መሰለኝ፣ “የጦርነቱ ፊሽካ ተነፍቷል” ያሉት፡፡
ምን ያድርጉ ብዙዎቹ የቡድኑ አባላት በፊሽካ የሚመራ የስፖርት ጨዋታ እንጅ በድሽቃ የሚካሄድ የሽምቅ ውጊያ የት ያውቁና…..
በዚህ አላዋቂነታቸውም በፊሽካ የተጀመረው ጦርነት ማሳረጊያው ወደ ዋሽንግተን የሚመልሰውን ዳገት መውጣት ሆነና አረፈው፡፡
ቁልቁለትና ዳገት መለየት ያልቻሉት፣ ፊሽካና ዲሽቃ መለየት ያቃታቸው ግንቦተኞች፣ ሲሄዱ እየፎከሩ የተንደረደሩትን ቁልቁለት ሲመለሱ እያቃሰቱ ወጥተውታል፡፡
እንደው ምሁር ነኝ ብለው ቢመጻደቁም ሰው የሚልዎትን አላዋቂነትዎን ግን ዶክተርዬ ቢሰሙኝ ጥሩ ነው፡፡
ድሮውንም ቁልቁለት በሌለበት ነው እንደረደራለሁ ያሉት፡፡ ለእርስዎና ለመሰሎችዎ አዲስ አበባ ለመድረስ ዳገት እንጅ ቁልቁለት ኖሮ አያውቅም ነበር፡፡
ድሮውንም “ያላዋቂ ሳሚ” አድርገውት እንጅ ከዳገትም በላይ ከፊትዎ ያለው ለባለ ፊሽካ መቼውንም የማይደፈር ተራራ ነው እያለ ነው - ዲያስፖራው፡፡
መቼም ዶክተር ብርሃኑ በሩ ጠቦዎት አብጠው እየፎከሩ ዘምተው፣ በመስኮት ሹልክ ብለው መግባትዎ ግን ብዙዎች ሙድ እንዲይዙብዎት አድርጓል፡፡ ደግሞ እኮ ያች አውሮፓ የተባለችውን ትልቅ አህጉር እንደመስኮት መጠቀምዎ ነው ጉዳዬን አዝናኝ ያደረገው፡፡
አውሮፓ ህብረት ምናምን ብለው ፎክረው ብራሰልስ ከርመው ከአስመራ እንደመጣ ሰው ይፎግራሉ እንዴ?
አንደው ምን አለበት፣ የእግድነት ጊዜዎን አራዝመው ያችን ዘመድዎን ባያስቸግሯት ኖሮ? አውሮፓም ቢሆን ጨለማ ክፍል ውስጥ ለወራት ይከብዳል እኮ! እውነቴን ነው፡፡ አውሮፓ ላይ እንዳይታዬ ከጨለማ ክፍል ውስጥ መግለጫ እየሰጡ፣ በራስዎ ፍቃድ እስረኛ ሆነው ባንድ ክፍል ውስጥ ተከልለው ይህን ያህል ወራት መቆየትዎ በራስ ላይ እንደመፍረድ ነው መቼስ፡፡
“ፈቃደኛ እስረኛ” ሆነው መቆየትዎ አስገራሚ ነው መቼስ፡፡ እርግጥ ነው ይህን ለምን እንደሚያደርጉት እኔ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ `የአርበኝነት` ግርማ ሞገስዎ እንዳይነካ እና ከዘመቻ ተመለሱ ለመባል እንደሆነ እረዳለሁ፡፡
ግንኮ ከወዳጅዎ ግብዣ በኋላ አስመራ እንዳልተመሱ ሁላችንም እናውቅ ነበር፡፡ እርግጥ ነው አንዳንዶቹን ትንሽ በፉገራዎ ሳያደናግሯቸው አልቀሩም፡፡ ምናልባትም ብራሰልስ እንደቆዬም የኢሳት ጥቃቅን “ጋዜጠኞችም” እንደማይነገራቸው አውቃለሁ፡፡
እዚህ ላይ አድማጭ ለምን ብሎ ከጠየቀ መልሱ “ይህ የግንቦት 7 ወታደራዊ የቅጥፈት ሚስጥር ነው” ይባላል፤ “ቶፕ ሴክሬት!” ብሎ እንዲረሽን ደርግ፣ የግንቦት 7 “ቶፕ ሴክሬት” ብሎ የሚጠብቃቸው እንዲህ አይነት ውሸቶችን ነው፡፡
እናም እውነታው፣ በቅድመ የቁልቁለት ጉዞ “ከዋሽንግተን ወደ አስመራ” ሲሄዱ በነ ሞላ አስግዶም (በፈረሰው ደምሂት አመራሮች) ግፊት ሲሆን፣
በድህረ ዳገት የመልስ ጉዞ ደግሞ “ከአስመራ - ብራሰልስ - ዋሽንግተን” በአና ጎሜዝ እርዳታ አማካኝነት ነው፡፡
እኔ እንደውም ዘመቻውን ሳስበው ከባህሪያቸው አንጻር ዶክተር ከሚገባቸው በላይ ዘምተው ቆይተዋል ባይ ነኝ፡፡ የቆዬት ከፈቃዳቸው ውጭ እንደሆነ ብረዳም ማለቴ ነው፡፡ እውነቴን ነው ዘመቻቸውን የምታቃልሉ ካላችሁ “አስተዋጽዋቸውን” ለማየት መስዋትነታቸውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንዴ! በዚያ ቆይታቸው እኮ ብዙ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡
ምንም እንኳን “ለዘማች አርበኛ” ዋናው ጉዳቱ መቁሰሉ እና መሰዋቱ ቢሆንም ዶክተር ብርሃኑም በምሁር አቅማቸው የሚገባቸውን ያህል መስዋእት ሆነዋል ባይ ነኝ፡፡
አንዴ የኢሳት ዋና ዜና ሆኖ ደጋፊዎቻቸውን ሲያስጨንቅ የነበረውን ዜና መቼም አድማጮቼ አትረሱትም፡፡
ባንድ ወቅት ሊቀመንበሩ የምግብ መመረዝ “መስዋትነት” አጋጥሟቸው ጭንቅ ጥብ ሆኖ እንደነበር እደሳችሁት እንዴ፡፡ በቃ ለግብራቸው፣ ለባህሪያቸው እና ለአቅማቸው የሚመጥን መስዋእትነት ከፍለው ተመልሰዋል፡፡ እንደተባለው ጦርነት ሜዳ ውስጥ ገብተው ተኩሰው የሚያታኩሱ ቢሆኑ ኖሮ በጦርነቱ ጥይት አሊያም በጉዞው እንቅፋት መታቸው ሲባል እንሰማ ነበር፡፡
ጦርነቱ ሆዱ ላይ ለሆነ የምግብ አርበኛ ግን ሊያጋጥመው የሚችለው ትልቁ መስዋእትነት ያው እንደተባለው የምግብ መመረዝ ብቻ ነው፡፡ ያኔ መስዋትነቱን ስንሰማ አንዳንዶቹ ይሉት የነበረውን ዛሬም አልረሳውም፣ “ዶክተርዬ አሜሪካ ሆነው ቢሆን ኖሮ መች ይሄ ይገጥማቸው ነበር” ይሉ ነበር፡፡ እውነት ነው፣ ሊቀመንበሩ የሳህን ማለቴ የተቋጠረ ምግብ በዘመኑ አጠራር ቴክ አወይ ብቻ ነበር የሚመቻቸው፡፡
ከአረብ ሃገር ምሳቸው ታስሮ በአስመራ አድርጎ ዋሽንግተን መጥቶ በልተውት ይስማማቸው ነበር - ድሮ ከአርበኝነታቸው ዘመን በፊት፡፡
ለዓመታት በዚህ ያልረኩት ዶክተር ብርሽ ግን ላይቭ ምግብ ላግኝ ብለው ተሸወዱ፡፡ ትኩስ የሻእቢያ ምግብ በቅርበት አልተስማማቸውም፡፡ የምግብ መመረዝ አመማቸው እና መስዋእትነታቸው በዜና ተነገረ፣ ጽንፈኛውን ሁሉ ከንፈር አማጠጠ፡፡
እንዴው እኒያ ሽማግሌው ፕሮፌሰር መክሸፍ ምናምን ብለው የጻፉትን ባያሳትሙት ኖሮ ይህንን ታሪክ ያካትቱት ነበር፡፡
“መክሸፍ እንደ አርበኛው ብርሃኑ” ቢሉን ጥሩ አና አሳማኝ እውነታ ያሳትሙ ነበር፡፡ እውነቴን ነው፣ በባዶ እግሩ እሾህ ቆንጥር ጋሬጣ ሳይሰጋ ከመድፍና ታንክ ጋር የተዋጋ አርበኛ ባፈራች ሃገር፣ ሴፍቲ ጫማ አድርጎ፣ ምግብ ላይ ሲዋጋ የሚወድቅ ተላላኪ “አርበኛ” ተባለባት፡፡ “መክሸፍ” ማለት ይሄ ነው፣ ፕሮፌሰር፡፡
አንዳንዴ አሁን መመለሳቸውን ከሰማሁ በኋላ ሳስበው ዶክተር ብርሃኑ ኤርትራ እያሉ የቴምር ዛፍ በትካዜ እያዬ የሚያንጎራጉሯት ዜማ ይህች ትመስለኛለች፣
“አወይ ዋሽንግተን ኢሳትዬ ሆይ፣
ሃገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ!!”
ለማንኛውም የዶክተር ብርሃኑ መመለስ ያስደነቃችሁ ካላችሁ እኔ ይሄ ብዙ የሚደንቅ እንዳልሆነ ቀደም ብዬም ነግሬያችኋለሁ፡፡
ከዚህ በፊት ዶክተሩ ለዘመቻ ነጋሪት እያስጎሰሙ በነበረበት ወቅትም በመልእክተ ሰለሞን ያልነውን ደግመን እናስታውሳችሁ፡፡ ነጋሪት ያልነውን ግልጽ ለማድረግ ግንቦተኞች ሲዘምቱ በሽለላና ቀረርቶ የሚጎሰመው ኢሳትን ለማለት ነው፡፡
ያኔ እኛ ይህንን ብለን ነበር “እመኑኝ ዶክተር ብርሃኑ የሄደው ለገንዘብ ቃርሚያ የፕሮግራም ግብዓት እንጅ እውነት እንደተባለው ህይወቱን ለትግል ሰጥቶ አይደለም፡፡ በሚቀጥለው አዲስ ዓመት ዋሽንግተን ተመልሶ እስኪ ትንሽ በፕሮፌሰርነት ማእረጌ ልስራበት” ማለቱ አይቀርም ብለን ነበር፡፡
እናም ይሄው እንዳልነው ጃንዋሪ በባተ በነጋታው ከብራሰልስ ዋሽንግተን ከች አለና ያልነውን እውነት አደረገው፡፡
እርግጥ ነው ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ መተንበይ ትልቅ እውቀት የሚጠይቅ አሊያም ነብይነትን ግድ የሚል አይደለም፡፡ ጽናት ራዲዬ ላይ አምና ከዘመቻው ማግስት ሊቀመንበሩ ይመለሳል ስንል ከሰውየውና ከቡድኑ መሰረታዊ ባህሪ በመነሳት ብቻ ነው፡፡
እናም ያልነው ሲሆን ለከሸፈው ዘመቻ መልስ የተሰጠው ሽፋን ደግሞ አስቂኝ ሆኖብኛል፡፡ “ለአጭር ጊዜ ተልእኮ ዶክተር ብርሃኑ ወደ ዋሽንግተን ተመልሰዋል”
ነው የተባለው፡፡
ደግነቱ ዛሬ ዶክተር ብርሽ የተመለሰው ተልእኮውን ጨርሶ ሳይሆን ለዬንቨርስቲው የመላው የፍቃድ ጊዜ በማለቁ ብቻ ነው፡፡
አይ ዘመን….ጦርነትም እንዲህ ሆነና አረፈው፡፡ ፍቃድ ሞልተው ባመት እረፍት የሚዘምቱበት አርበኝነት በነ ብርሃኑ ነጋ ትግል ውስጥ አየንና መክሸፋቸው ጥጉ የት ድረስ እንደሆነ አሳዬን፡፡
ቀድመው የመጡት ተመላሾች ደግሞ ሲሉት የነበረውን እናስታውስ “በአስመራ የነበረኝን ተልእኮ ጨርሼ ተመልሻለሁ” ነበር የሚሉት፡፡  እና ሁሉም ሁሉም ያጫጭር ጊዜ ተልእኳቸውን እየፈፀሙ ያመት እረፍታቸው ሲያልቅባቸው ተመልሰው አንድ ሰው ብቻ እዚያ ቀረ፡፡
በጣም የሚገርመው ግን ሲዘምቱ አጭበርብረው የሞሉት የህክምና ፍቃድ ሳይሆን “በአጭር ጊዜ አራት ሊሎ ታገኙናላችሁ አምስት አምስት መቶ ዶላር አዋጡ” ማለታቸው ነው አስደናቂው ነገር፡፡
ለማንኛውም ሁሉም ግንቦተኞች እና አመራሮቻቸው ተልእኳቸውን እየጨረሱ ተመልሰው አሁን የቀረው አንድ አመራር ብቻ ነው፡፡ እሱም ብቻውን ስቱዲዬ ውስጥ ለዘመቱት አርበኞች ስንቅና ወሬ ከመቋጠር የዘለለ የመሪነት ሚና አይኖረውም፡፡ ያም ሆኖ ሰውዬው ድርጅቱ እስኪቀበር ድረስ የመሪነት ሚናው አሁንም ከዶክተሩም በላይ ሆኖ የሚቀጥል ነው፡፡ አለቃና የፋይናንስ ምንጭ ነውና ቁልፉ በእጁ ነው፡፡
ኤርትራ የቀረው የግንቦት 7 አመራር ማእረግ ያልተሰጠው የቡድኑ ሊቀመንበር ሽማግሌው ኢሳያስ አፈወርቂ ብቻ ነው፡፡
እርስዎስ መቼ ነው የሚመለሱት ጌታው!!!!

03161063
Today
Yesterday
This Month
Last Month
All days
2983
4118
86576
75600
3161063

Since April 1, 2014

Photo Gallery